ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ55 ሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመት ሰጡ

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ መልክ ላዋቀሩት ካቢኔ የ55 ሚንስትር ዴኤታዎች ሹመት ሰጡ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ ባደረሰው መረጃ መሰረት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ ከፍያለው ተፈራ፣ አቶ ዘይኑ ጀማል፣ ዶክተር ስዩም መስፍን እና ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ሆነው ተሹመዋል። አምባሳደር ሌላአለም ገብረዮሃንስ እና አቶ ፍስሀ ወልደሰንበት የመከላካያ ሚኒስቴር፤ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ፣ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል እና ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሆነዋል። ለገንዘብ ሚኒስቴር አቶ አድማሱ ነበበ እና አቶ ኢዮብ ተካልኝ፤ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ገለታ ስዩም፣ አቶ አድማሱ አንጎ እና ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ ለግብርና ሚኒስቴር ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስ፣ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ፣ አቶ ሳኒ ረዲ እና ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በሚኒስትር ዴኤታነት ተሹመዋል። አቶ ዮሐንስ ድንቅ አየሁ፣ አቶ እሸቴ አስፋው እና አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሲሆኑ፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ዶክተር ሹመቴ ግዛው፣ አቶ ሲሳይ ቶላና አቶ ጀማል በከር በሚኒስትር ዴኤታነት ተሹመውለታል። ወይዘሮ ሕይወት ሞሲሳ፣ አምባሳደር ሀሰን አቡዱልቃድር፣ አቶ ነጋ በርኸ እና ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች ናቸው። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ አቶ ካሊድ አብዱራህማንና አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር፤ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ዶክተር አብርሃ አዱኛ፣ ዶክተር ነጋሽ ዋቅሻውና ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሀና ሆነዋል። አቶ አሰፋ ኩምሳና ዶክተር ኮንግ ቱትላም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፤ አቶ መሀመድ አህመዲንና ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ የትምህርት ሚኒስቴር፤ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሳና ዶክተር አብዲዋሳ አብዱላሂ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ነው የተሾሙት። ወይዘሮ ሳህርላ አብዱላሒ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ፤ ወይዘሮ አለሚቱ ኡመድና ወይዘሮ ስመኝ ውቤ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታዎች ሆነዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ ጌታሁን አብዲሳና ወይዘሮ አየለች እሸቴ፤ የባህልና ቱሪዝም ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፣ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረትና አቶ ሐብታሙ ሲሳይ፤ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታዎች ደግሞ አቶ ዘመዴ ተፈራ፣ አቶ መሀመድ አብዱ አህመድ፣ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሔርና ወይዘሮ ምህረት ምንአሰብ ናቸው። አቶ ጌታቸው አደም የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም