ቀጥታ፡

የዘንድሮው የብሄር ሔረሰቦች ቀን ኢትዮያዊ ማንነት ጎልቶ የሚከበርበት በዓል ይሆናል-የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 በመጪው ሕዳር ወር ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊ ማንነት ጎልቶ የሚከበርበት በዓል እንደሚሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና በዓሉን የምታስተናግደው አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ሕዳር 29 ቀን የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ላለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት የተከበሩትን በዓላት ደካማና ጠንካራ ጎን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል። በዚህም በዓሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረ ብሄራዊነት ደምቆ የታየበት፣ ሁሉም ብሄረሰቦች በእኩልነት ማንነታቸውን ያሳዩበት፣ በዓሉን ባከበሩ የአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች መሰረተ ልማት የተስፋፋበትና በህዝቦች መካከል ትውውቅ የተፈጠረበት መሆኑ ጠንካራ ጎን እንደነበር የዳሰሳ ጥናቱ ማሳየቱን ገልጸዋል። ይሁንና በተለይ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሲገመገም ኢትዮጵያዊ ማንነት ከብሄራዊ ማንነት አቀናጅቶ ከመሄድ አንጻር ሰፊ ክፍተት እንደነበረበት ጠቅሰዋል። 'ብሔራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ተነጣጥለው ኢትዮጵያን ማስቀጠል አይቻልም' ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፣ ባለፉት ዓመታት ለኢትዮጵያዊ ማንነነት ከብሄራዊ ማንነት ጋር እኩል እውቅና ተሰጥቶት ባለመተግበሩ አሁን ለሚስተዋለው የሰላምና መረጋጋት መደፍረስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል። በዓሉ ሲከበር በህዝቦች መካከል የነበረውን የመከባበር፣ መቻቻል፣ መፈቃቀር እሴቶች በማጠናከር አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት በሚፈለገው ልክ አለመሰራቱን ጠቅሰዋል። ስለሆነም በዚህ ዓመት ከወትሮው በተለየ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በማጉላት እንደሚከበር በመግለጫው ላይ ተናግረዋል። አሁን ላይ በብሄሮች መካከል፣ ግጭት፣ መጠራረጠር፣ በማንነት መፈናቀልና ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በዓሉ በህዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት፣ ፍቅርና መቻቻልን በሚያጎላ፣ ሰላምና መረጋጋት በሚያሰፍን መልኩ አንደሚከበር ተናግረዋል። በተለይም መቃቃርና ጥላቻን በማስወገድ አንድነትን አጉልቶ ልዩነቱን አጥብቦ ለመሄድ በአስተሳስብ ላይ ሰፊ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዓሉ በቀጣይ ሲከበርም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ሊያጠናክር በሚችልበት ሁኔታ እንደሚሆን ተናግረዋል። የኃይማኖት ተቋማት፣ የጎሳ መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሚዲያ ተቋማት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱም ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በበኩላቸው ለ13ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አከባበር ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱን ጠቁመዋል። ''አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ከተማ ናት'' ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች ለአዲስ አበባ ጥሩ ትዝታ እንዲኖራቸው በሚያደርግ ሁኔታ እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ የከተማዋ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚጎላበት፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት የሚንጸባርቅበትና በአገሪቱ ካለው ለውጥ ተደማሪ እሴት በሚሆን መልኩ እንደሚከበር አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም