ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የተደረገልን ቤተሰባዊ አቀባበል ከጠበቅነው በላይ ነው---የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተማሪዎች

ባህር ዳር ጥቅምት 14/2011 በባህር ዳር ከተማ የተደረገልን ቤተሰባዊ አቀባበል ከጠበቅነው በላይ ነው ሲሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ። ወደ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ለሚገቡ ከ6 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች በአምስት መግቢያ በሮች ትራንስፖርት በማዘጋጀት አቀባበል እያደረገ መሆኑንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል። ከትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የመጣው ተማሪ ገብረዮሐንስ ታደለ "ወደዚህ ከመምጣታችን በፊት በሰማናቸው አንዳንድ ወሬዎች ከወላጆቻችንና ከጓደኞቻችን ሳይቀር የስጋት ስሜት ተፈጥሮ ነበር" ብሏል። "በላልይበላ በኩል መጥተን ባህር ዳር ከተማ ስንገባ በወሬ እንደሰማነውና እንደፈራነው ሳይሆን ሰዎች ከጠበቅነው በላይ ጥሩ አቀባበል አድርገውልናል" ሲልም ተናግሯል። በቀጣይም ከተለያዩ ክልሎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር የባህል ልውውጥ በማድረግ፣ እርስ በዕርስ ያለውን ዕውቀት በመጋራትና ጠንክሮ በመማር የተሻለ ዕውቀት ይዞ ለመውጣት ማቀዱን ገልጿል። የመማር ማስተማሩ ድባብ ሰላማዊ እንዲሆን ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ነው የተናገረው። ከባህር ዳር አየር ማረፊያ እንደደረሰች በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀ መኪና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ወደዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንደመጣች የገለጸችው ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ የመጣችው ተማሪ ህይወት ደገፉ ናት። " የደረሰኝ የህክምና ትምህርት በመሆኑ ጠንክሬ በመማርና በማጥናት ጥሩ ዕውቀት ይዤ ትምህርቴን በማጠናቀቅ ሀገሬንና ወገኔን ለማገልገል ትልቅ ህልም አለኝ " ብላለች። ከአዲስ አበባ የመጣው ተማሪ ዕውነቱ ተሰማ በበኩሉ "እንዲህ አይነት አቀባበል ይደረጋል ብዬ አላሰብኩም፣ ከቤቴ ስነሳ ዩኒቨርሲቲው እስክገባ ድረስ መጉላላት ይገጥመኝ ይሆናል ብዬ ሰግቼ ነበር" ሲል ተናግሯል። የመማር ማስተማሩ ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን በሁሉም ዘርፍ የድርሻውን ለማበርከት መዘጋጀቱንም ነው ተማሪ ዕውነቱ የገለጸው። ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የመጡ ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲው እየገቡ ያሉት ከሰኞ ጀምሮ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሕብረት አባል ተማሪ አለበል ዋለ ነው። አዲስ ተማሪዎች ለዘረፋና ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ኮሚቴ ተዋቅሮ አቀባበል በማድረግ ወደየተመደቡበት ግቢ ያለምንም ችግር እንዲገቡ በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድቷል። የዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአቀባበል አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዘውዱ ዕምሩ በበኩላቸው ለአዲስ ተማሪዎች በባህር ዳር ከተማ 5 ቦታዎች ላይ አቀባበል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በዘንዘልማ፣ በይባብ፣ በአየር ማረፊያ፣ በአዲሱና አሮጌው መናኽሪያ ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ባቋቋመው የአቀባበል ኮሚቴ አማካኝነት እስከምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ተማሪዎችን እየተቀበሉ መሆናቸውን ተናግርዋል። "የተቋቋመው ኮሚቴ ለአዲስ ተማሪዎች አቀባበል ከማድረግ ባለፈ በቀጣይም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ገለጻ በመስጠት የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ይሰራል" ብለዋል። ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችን ጨምሮ መደበኛና መደበኛ ባልሆነ የትምህርት መርሃ ግብር ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም