እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት ሊያባብስ ይችላል-ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት ሊያባብስ ይችላል-ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነትን ሊያባበስ ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ የግብርና ሚኒስቴር አሳሳበ። ዝናቡ እስካሁን በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት አለማድረሱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም በዋና ዋና ሰብሎች ከ375 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል። የተደረገው የቅድመ ዝግጅት ስራና የአየሩ ሁኔታ ለሰብል ተስማሚ በመሆኑ በመኸር ወቅት የታሰበውን ያህል ምርት እንደሚገኝም ቅድመ ትንበያዎች ያሳያሉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን በአገሪቷ ከሚመረተው ምርት በተለያዩ ምክንያቶች ከማሳ እስከ ጎተራ ድረስ በአማካኝ ከ25 እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት ያጋጥማል። የምርቱ አያያዝ የተሻለ ቢሆንም ሰሞኑን በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ነው የሚኒስቴሩ የፕሮሞሽንና ዶክመንቴሽን ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ደንታሞ የሚናገሩት። ከሚጠበቀው አጠቃላይ ምርት ውስጥም እስካሁን 621 ሺህ ኩንታል መሰብሰቡን ገልጸዋል። አርሶ አደሩ አስቀድሞ ምርቱን በመሰብሰብና ዝናብ በማይደርስባቸው አካባቢዎች በማከማቸት ከአላስፈላጊ የምርት ብክነት እንዲጠብቅም አሳስበዋል። ዝናቡ የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽና ምርትም እንዳይባክን አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የመከላከያ ሰራዊትና በየደረጃው ያሉ አመራሮች እንደዚሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርበርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል። ዝናቡ እስካሁን በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት አለማድረሱን የተናገሩት ቡድን መሪው የዝናቡ ሁኔታ ቀጣይነት ካለው ግን በምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርሰ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል። በሌላ በኩል በደጋማው የአገሪቱ አካባቢዎች ዝናቡ ለቀጣይ እርሻ ስራና ሰብል ልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው አርሶ አደሩ የሚያገኘውን እርጥበት በአግባቡ እንዲጠቀም ጠቁመዋል። የብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አቡበከረ አንዳሉት በቀጣዮቹ አስር ቀናት በደቡባዊ የአገሪቷ ተፋሰሶች ከፍተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያው መረጃ ያሳያል። በተጨማሪም በአብዛኛው የላይኛውና አንዳንድ የላይኛው አዋሽ፣ የታችኛው የዋቢ ሸበሌና የኦጋዴን ተፋሶሶች ወቅቱን ያልጠበቅ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልና የቀሩት የአገሪቷ ተፋሰሶችም ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩም ገልጿል። በሌላ በኩል በአንዳንድ የአገሪቷ ክፍሎች የሚጥለው ዝናብ በአካባቢው ለሚደረገው የማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችም ለግጦሽ፣ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።