ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ሙሉ የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ እንደሚያስፈልግ በጥናት ተመላከተ

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ሙሉ የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስጠናው ጥናት አመለከተ። የፌዴሬሽኑ አዲሱ አመራር በእግር ኳሱ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና መልካም ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በጥናት የተደገፈ ስራ ለመስራት ተዘጋጅቷል። በጥናቱ አሁን ባለው የፌዴሬሽኑ ቁመና በጥንካሬ የሚጠቀሱ አሰራሮች አለመኖራቸው ተለይቷል። የተዳከመውን እግር ኳስ ለማከም ካስፈለገ የፌዴሬሽኑን አደረጃጀትና አሰራር ሙሉ በሙሉ በአዲስ መልክ ማዋቀር እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አመላክቷል። የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ሰራተኞች በአቅምና ችሎታ አለመመደብ የፌዴሬሽኑ ችግር እንደሆነ ተገልጿል። በሌላ በኩል በእግር ኳስ ልማት ላይ የተሰራ አጥጋቢ ስራ አለመኖሩን ያመላከተው ጥናቱ ለውጥ ለማምጣት ጥገናዊ ሳይሆን ስርነቀል አደረጃጀትና መዋቅር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። ፌዴሬሽኑ ተከታታይነት ያለው የአሰልጣኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ላይ  ክፍተት እንዳለበት ተመላክቷል። ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በጥናቱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም