ወላጅ ያጡ ሕፃናትን በራስ አቅም መደገፍና መንከባከብ ይገባል-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን - ኢዜአ አማርኛ
ወላጅ ያጡ ሕፃናትን በራስ አቅም መደገፍና መንከባከብ ይገባል-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 የውጭ ተረጂነትን በመቀነስ ወላጅ ያጡ ሕፃናትን በራስ አቅም መደገፍና መንከባከብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለጸች። በቤተክርስቲያኗ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት "የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት 45ኛ ዓመታት የልማት ጉዞና መጪው የለውጥ ጉዳይ" በሚል ርዕስ ለአምስት ቀን የሚቆይ ዐውደ ርዕይ በዛሬው እለት ተከፍቷል። በዚህ ጊዜ የቅዱስ ፓትሪያርኩ ተወካይና የሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ቤተክርስቲያኗ ወላጅ አጥ ሕፃናትን ለቁምነገር ለማብቃትና ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋዊያንን ለመርዳት በርካታ ተግባራት ማከናወኗን ገልጸዋል። በዚህም ባለፉት 45 ዓመታት በአገር ውስጥ በሚደረጉ የአዕምሮ፣ የአካል፣ የመንፈስና የስነ ምግባር እንቅስቃሴ ረገድ ባደረገችው አስተዋጽኦ 40 ሺህ ህፃናትን በመንከባከብና በመደገፍ ለቁም ነገር ማብቃት ችላለች ብለዋል። በቀጣይም ወላጅ ያጡና በየጎዳናው ወድቀው የሚገኙ ህፃናት ለአገራቸው በጎ ዜጋ እንዲሆኑ የውጭ ድጋፍን በመቀነስ በራስ አቅምና ከአገር ውስጥ ሃብት በማመንጨት መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል። ለዚህም ምዕመኑ የበኩሉን አስተዋጾኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ሌላው የሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስደተኞችንና ማንኛውንም ሰው በዘር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ ሳትለይ ተቀብላ በማስተናገድ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ባለቤት ነች ብለዋል። በዚህም ባለፉት 45 ዓመታት ቤተክርስቲያኗ ባላት አቅም በትምህርት ፣ በሆስፒታልና በመጠለያ አቅርቦትና በመሳሰሉት ምግባረ-ሰናይ ተግባራት ከፍተኛ ተግባር አከናውናለች። ይህን ተግባር በቀጣይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀትና አሰራር አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል ብለዋል። የቤተክርስቲያኗ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ቄስ ሳምሶን በቀለ ደግሞ ድርጅቱ ሀብት ከውጭ በማሰባሰብ እየሰራ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይ ግን ሀብትን ከሀገር ውስጥ ለማመንጨትና በስፋት ለመንቀሳቀስ ረቂቅ መመሪያና አደረጃጀት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ይህም ህፃናትን በእንክብካቤ ከማሳደግና ለቁም ነገር ከማብቃት ባለፈ አረጋዊያንን ለመደገፍና በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩትን ዜጎች ህይወት ለመቀየር ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል። በተለይም ተመሳሳይ ስራ ከሚሰሩ ምግባረ-ሰናይ ተቋማት ጋር በመቀናጀት አቅም ያለው ሰው ልጆችን እንዲደግፍና እንዲከታተል ለማድረግም መሆኑን አክለዋል። አውደ ርዕዩ እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን ከጥቅምት 19 እስከ 20 ደግሞ በተመረጡና በተለዩ ርዕሶች ላይ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።