ቀጥታ፡

በህንድ የሚገኙ የቢዝነስ ተቋማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 በህንድ የሚገኙ አርባ የሚሆኑ የቢዝነስ ተቋማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በኮንስትራከሽን፣ በፋርማሲ፣ በጨርቃ ጨርቅና በሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ተቋማቱ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው። የውጭ ባለሃብቶችን በአዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰማሩ በማድረግ የንግድ ጉድለቱን ለመሙላት ኢትዮጵያ የምታገኛቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች በተገቢው መንገድ እንድትጠቀም ለማስቻል ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። ሚኒስቴሩ በተለያዩ የኢንቨሰትመንት ስራዎች ለመሳተፍ ከህንድ አገር ከመጡ ባለሃብቶችና የቢዝነስ ተቋማት የልዑክ ቡድን ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ወቅት የሚኒስቴሩ የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ መስፍን ገብረማሪያም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጰያ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። በዋናነትም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ዘርፉንና የወጪ ገቢ ንግዱን ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል። ባለሃብቶቹና የቢዝነስ ተቋማቱ ተወካይ ልዑካን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ መደረጉን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን አስረድተዋል። ባለሃብቶቹ ከተለያዩ ዘርፎች የተወጣጡ በመሆናቸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ለማድረግ ውይይት መደረጉንና ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ከህንድ አገር መጥተው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚገኙ የቢዝነስ ተቋማት ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይህም ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሳተፉ ማድረጉ አገሪቱ የወጪ ንግድን በማሳደግ በንግዱ ዘርፍ የሚታየውን ጉድለት ለመሙላት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። የህንድ ባለሃብቶችና የቢዝነስ ተቋማት በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በህንድ የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ መስፍን በቀጣይም ማብራሪያ በሚፈልጉባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት ሚኒስቴሩም ሆነ ቆንስላው ዝግጁ እንደሆኑ አብራርተዋል። በህንድ አገር የጂያን ኢንተርናሽናል ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ ሳቲሽ ሂራን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የጀመረቻቸው እንቅሰቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ''እኛም አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በመመልከት በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ነው የመጣነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያና ህንድ በንግድና ኢንቨስትመንት የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ የህንድ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ 600 የሚሆኑ የህንድ የቢዝነስ ተቋማት ህጋዊ ፈቃድ ወስደው በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም