ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ነገ የስራ መልቀቂያ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በነገው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ የስራ መልቀቂያ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። የአስቸኳይ ስብሰባው ዋና አጀንዳ የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን የስራ መልቀቂያ መቀበልና አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጥ እንደሚሆን ተገልጿል። ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ሶስተኛው ፕሬዚዳንትም ናቸው። ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ አርጆ ከተማ በ1949 ዓ.ም ነው የተወለዱት፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቻይና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና፣ ሁለተኛውን በህግና ዲፕሎማሲ ከአሜሪካ፣ 3ኛ ዲግሪያቸውን ከቻይና ቤጂንግ ዩኒቨርስቲ በህግ አግኝተዋል። ፕሬዝዳንቱ በጃፓንና በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ ከ1993-1994 ዓ.ም የግብርና ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 1994-1998 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነውም አገልግለዋል። በፕሬዝዳንትነት እስከተመረጡበት ጊዜም በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነበሩ። ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በተለያዩ መስኮች ያከናወኑና በመምህርነትም ያገለገሉ ሲሆን ከአገር ውስጥ አማርኛና ኦሮምኛ ከውጭ ደግሞ እንግሊዝኛ፣ ቻይንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን መናገርና መጻፍ ይችላሉ። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት አንድ ግለሰብ ከሁለት ጊዜ በላይ በርዕሰ ብሔርነት ሊመረጥ እንደማይችል ይደነግጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም