መከላከያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሆነ

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 መከላከያ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሆነ። ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የዋንጫ ጨዋታ መከላከያ ጅማ አባ ጅፋርን በመለያ ምት በማሸነፍ ሻምፒዮን ለመሆን ችሏል። ሁለቱ ክለቦች በመደበኛው 90 ደቂቃ  ጨዋታቸውን 1 ለ 1 ያጠናቀቁ ሲሆን ለመከላከያ ሳሙኤል ታዬ፣ እንዲሁም ለጅማ አባ ጅፋር ኤሊያስ ማሞ ግቦቹን አስቆጥረዋል። በዚህም አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት  ያመሩ ሲሆን በዚህም መከላከያ ጅማ አባ ጅፋርን 4 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በጨዋታው የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰ የጅማ አባ ጅፋርን ተጫዋች  በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊዎች የሚገናኙበት የዋንጫ ጨዋታ ነው። ጅማ አባ ጅፋር የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ በመሆኑም በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ መከላከያ ደግሞ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ በመሆኑ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉም ይታወቃል። የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ እንደሚጀመር ከፌዴሬሽኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም