የኦሮሚያ ልማት ማህበር ለህበረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚሰራቸውን ልማቶች ተጠናክረው እንደቀጠሉ ናቸው

120
አዳማ ጥቅምት 13/2011 የክልሉን ሕብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  በትምህርት፣ በጤናና በንፁ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ  እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠሉን የኦሮሚያ ልማት ማህበር ገለጸ። የኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ ለኢዜአ እንደገለጹት በመንግስት አቅም በማይደረስባቸው የክልሉ አካባቢዎች  የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማህበሩ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አቶ ደጀኔ እንዳሉት ማህበሩ ባለፉት ዓመታት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለክልሉ ህዝብ ከ3 ሺህ በላይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርት፣ የጤናና የንጹ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎችን አከናውኗል። በእዚህም በ320 የክልሉ ወረዳዎች 731 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከ200 በላይ የጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች፣1ሺህ 700 የንጹ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል። በዘንድሮ ዓመት ማህበሩ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በአዳማ ከተማ ባለ12 ወለል ሁለገብ የገበያ ማዕከል ህንጻ እያስገነባ መሆኑን ነው የገለጹት። በተመሳሳይ በጉደርና ለገ ጣፎ ለገዳዲ እየተገነቡ ያሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሜታ ሮቢ፣ ጂዳ፣ አብቹና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በማከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ማህበሩ ባስገነባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙት ተማሪዎች ውስጥ 39 ሺህ የሚሆኑት ቁጠባ እንዲጀምሩ በመደረጉ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን ተናግረዋል። ማህብሩ ከ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አባላት ማፍራት መቻሉን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የማህበሩን ስኬታማ ስራ ለማጠናከር 131 ሚለዮን ብር የነበረውን የአባላቱን ዓመታዊ መዋጮ ወደ 300 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል። በክልሉ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አጠናክረን ለማስቀጠል በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በቢሾፍቱ፣ ሻሻመኔ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ አምቦ፣ አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የገቢ ማስገኛ ሁለገብ የንግድ ተቋማትን በማስገንባት ማህበሩ ከአባላት መዋጮ ጥገኝነት ለማላቀቅና ራሱን እንዲችል ለማድረግ መታቀዱንም አቶ ደጀኔ ኢቲቻ ጨቁመዋል። ማህበሩ የመንግስት አቅም በማይደርስበት አካባቢ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ የቦርድ አባልና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ናቸው። እየተገነቡ ካሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ በክልሉ 20 ዞኖች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የኦልማ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለማደረጃት ማህበሩ እያደረገ ላለው ጥረት መንግስት የራሱን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። "በዚህም ቤተ ሙከራዎችን፣ የአይሲቲ ማእከላት፣ ቤተሙከራዎች፣ የመማሪያ ክፍሎችና ቁሳቁሶችን በበቂ ሁኔታ የማሟላት ሥራ ላይ በጋራ እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል። "የኦሮሚያ ልማት ማህበር አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በግብአት ማደረጃቱ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንድናገኝና በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤታማ አድርጎናል" ሲል የገለጸው ደግሞ የአዳማ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኑስበር ዱጉማ ነው። የማህበሩ ድጋፍ በትምህርት ጥራት ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በቀጣይም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም