የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ይፈታ… የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት - ኢዜአ አማርኛ
የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ይፈታ… የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት
ባሀር ዳር ጥቅምት 13/2011 የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባው የአማራ ክልል መንግሥት አሳሳበ። የክልሉ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በአማራና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል። በተለይም ከራያ አላማጣ ህዝብ ማንነት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በተከሰተ ግጭት ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ከመጥፋቱም በላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል። እንዲሁም ከወልቃይት አካባቢ ከማንነት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመረጋጋት ዜጎች በገዛ አገራቸው የመፈናቀል አደጋ ደርሶባቸው በጎንደር ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ዜጎች ለእንግልትም ሆነ ለከፋ ጉዳት ሳይጋለጡ ሕገ መንግሥቱን መሰረት ባደረገ አግባብ ህዝቡን በማነጋገርና የራሱን ዕድል እንዲወስን መብቱን በማክበር እንዲፈታ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ በኢህአዴግ ጉባዔዎች አቅጣጫ መቀመጡ መግለጫው አስታውሷል። ከግጭትና መፈናቀል የሚጠቀም አንዳችም አካል ባለመኖሩ ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት በማድረግ ሕገ-መንግሥቱ ላይ በመመስረት መፍትሄ መስጠት እንጂ፤ የኃይል እርምጃ መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል። አንዳንድ ወገኖች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ለሚፈጠረው ችግር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን መክሰሳቸው መሠረት ቢስ ውንጀላ ነው ያለው መግለጫው፤ የክልሉ መንግሥት ይህንኑ ከእውነት የራቀና ኃላፊነት የጐደለውን ክስ አይቀበለውም ብሏል፡፡ በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ህጋዊና ሰላማዊ ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። እንዲሁም በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስቧል። ሙሉ መግለጫው የሚከተለው ነው ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ ባለፉት ዓመታት በክልላችንም ሆነ በሀገራችን ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ ግጭቶች ካደረሱብን ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፓለቲካዊ ኪሳራ ለመወጣት በተደረገው ትግል በመላ ሀገራችንና ክልላችን የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ብሔራዊ ክልል ከትግራይ ብሔራዊ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የወልቃይትና ራያ አላማጣ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰላም መታወክ እየገጠመ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ወልቃይት አካባቢ በማንነታችን ብቻ ጥቃት ደረሰብን ያሉ የወልቃይት አማራዎች ተፈናቅለው በጐንደር ከተማ የሰፈሩ ሲሆን በሌላ በኩል በራያ አላማጣ በተፈጠረው ግጭት በሰው ህይወትም ጭምር ጉዳት አድርሷል፡፡ በተከሰተው ግጭት በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የተሰማውን ጥልቅ ኅዘን ይገልፃል፡፡ የተከሰተው ግጭት መነሻው የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሲሆን ይህንን ጥያቄ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ህገ-መንግስታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ አሁንም ቢሆን መፍትሄው ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት በማድረግ ህገ-መንግስቱ ላይ በመመስረት መፍትሄ መስጠት እንጂ የኃይል እርምጃ መውሰድ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በአንድ ክልል የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ለአጐራባች አካባቢዎች መትረፉ አይቀርምና የሰሞኑ የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ችግር ለክልላችንም ትልቅ የፀጥታ ስጋት ሆኗል፡፡ ከዚህ ሌላም አንዳንድ ወገኖች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚፈጠረው ችግር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መክሰሳቸው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ መሠረት ቢስ ውንጀላ ነው፡፡ በመሆኑም የክልላችን መንግስት ይህንንን ከእውነት የራቀ እና ኃላፊነት የጐደለውን ክስ አይቀበለውም፡፡ በአዋሳኝ ክልሎች የሚፈጠረው ግጭት የሌላ ክልል ጉዳይ ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ተሻጋሪነት ያለው ሁላችንንም የሚያውክ የሰላም ጠንቅ ነው፡፡ የዜጐች ጥያቄም በህገ-መንግስታዊ መንገድ ብቻ መልስ ማግኘት ይገባዋል፡፡ በመሆኑ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ህጋዊና ሰላማዊ ጥረት ሁሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን እያረጋገጥን በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባህር ዳር