በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ… - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ…
ምህረት አንዱዓለም/ኢዜአ/ “ኢትዮጵያውያን በዓለም አጽናፍ ኢትዮጵያን ይዘው ይዞራሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ከደማቸው ጋር የተዋሃደ ከልባቸው ጋር የታተመች ሀገር በመሆኗ።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት ወቅት የበርካቶችን ልብ የገዛ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ ንግግራቸው መላ ኢትዮጰያውያንን የሚያነቃቃ ቃል ያሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ምክንያት ከሀገር ወጥተው በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከትም እንዲህ ብለው ነበር። “በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ብሎ ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል፤ ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ እንጅ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ አታወጧትም የሚባለው ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ በልቀታችሁና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ ጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡ በኋላ የአንድነት ንቅናቄዎችን በንግግሮቻቸውና በተግባሮቻቸው እያስተሳሰሩ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ የማድረግ ዓላማ ሰንቀው በሃምሌ ወር መጨረሻ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ ወደ ልዕለ ሃያሏ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ጉዞ ጀመሩ። በአሜሪካ በነበራቸው የአንድ ሳምንት ቆይታ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎስ አንጀለስ እና በሚኔሶታ ከተሞች በሺዎች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ”ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ ” በሚል መርህ በርካታ ውይይቶችን አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሽንግተን ላይ መፍረስ የጀመረው የጥል ግድግዳ ሎስ አንጀለስ ላይ ሙሉ ለሙሉ መፍረሱን በማሳወቅ ሚኔሶታ ላይ የጥላቻ ግንቡን ፍርስራሽ በጋራ በማጽዳት ድልድዩን የመገንባት ስራ መጀመሩን አብስረዋል። ዶክተር ዐቢይ ድልድይ የመገንባት ጉዞውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ለሁለት ከተከፈለበት ወደ አንድ እንዲዋሃድ ያደረጉት ጥረትም ተጠቃሽ ነው። ይህን ተከትሎም በስደት ላይ የነበሩት አራተኛው የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል። ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን የመገንባት ጉዞ ከቤተ ክርስቲያኗ የሲኖዶስ ውህደት ባሻገር የፖለቲከኞች ይቅር መባባል የታየበትና የጥላቻ ጉዞ የተዘጋበትን አጋጣሚ አሳይቶናል። ዶክተር ዐቢይ በዋሽንግተን ዲሲ ከታማኝ በየነ እና በሚኔሶታ ከጀዋር መሃመድ ጋር በመተቃቀፍ የጥል ግድግዳን የማፍረስና የፍቅር ድልድዩን የመገንባት ተምሳሌትን በተግባር ማሳየታቸውም የወራት ትውስታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ዲሲና ሎስአንጀለስ ከተሞች በደረሱባቸው ዕለታት ”የኢትዮጵያውያን ቀን” እየተባሉ በየዓመቱ እንዲከበሩ በከንቲባዎቻቸው በኩል ውሳኔው ይፋ መሆኑም እንዲሁ ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ዋሽንግተን ላይ ኢትዮጵያውያኑን ሰብስበው ንግግር ባደረጉበት ወቅት “ኢትዮጵያዊነት ከደማችን ጋር የተዋሃደ ከአጥንታችን ጋር የፀና መሆኑን ዋሽንግተን ምስክር ትሆናለች” ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ ያሳዩት ስሜት እውነትም ኢትዮጵያን በልባቸው ይዘው እንደሚኖሩ ማሳያ ነበር። ዶክተር ዐቢይ ለሁላችንም የምትበቃ አንዲት ታላቅ ሀገር በጋራ እንገንባ በሚል በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበው የስድስት ቀናት ጉዟቸውን አጠናቅቀው ተመልሰዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የማግኘት ጉዞ በአሜሪካ ተጀመረ እንጂ በሌላውም ክፍለ ዓለማት ቀጥሏል። ጥቂት ወራትን ተሻግሮ እነሆ ጥቅምት ላይ ስንደርስ በመጪው ሰኞ አውሮፓ ላይ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር የመሰባሰቢያው የአንድነት ድንኳኑ እየተዘጋጀ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም በጀርመኗ ፍራንክፈርት ከመላው አውሮፓ ከተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ጋር ይገናኛሉ። አሜሪካ ላይ ”ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ ”በሚል የተጀመረው ጉዞ “አንድ ሁነን እንነሳ ነገን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ ፍራንክፈርት ላይ ኢትዮጵያውያኑን አሰባስቦ በሀገሪቱ ስላሉ እንቅስቃሴዎች ጠንካራ ሀገር ስለመገንባት እንዲመክሩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜሪከል በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት በሁለቱ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለቱ መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ዶክተር ዐቢይ በመላው አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለመምከር ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን ነው ቃል አቀባዩ የጠቆሙት። በጀርመኗ ከተማ ፍራንክፈርት ለሚኖረው የኢትዮጵያውያን የአንድነት መድረክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ዝግጅቶችን እያደረገ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ናት ያሉት ቃል አቀባዩ፥ የይቅር ባይነት፣ የአንድነትና የህብረት እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለችም ብለዋል። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ በሀገር ውስጥ ያለውን ዜጋ ብቻ ይዞ መስራት “ምን ተይዞ ጉዞ” በመሆኑ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሉት ቃል አቀባዩ፥ በውጭ ሀገር የሚኖሩ 3 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የሌሉበት የሀገር ግንባታ ጥረት ስኬታማ አይሆንም ነው ያሉት። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ የሀገር ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ስለሀገራቸው አብሮ ለመምከር ወደ አውሮፓ እንደሚጓዙ ገልጸዋል። አሜሪካ ላይ ድልድይ በመገንባት የተጀመረው የአንድነት ጉዞ በሀገር ቤት እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የነገዋን ሀገር የሚገነቡበትን ዓላማ በመያዝ ፍራንክፈርት ላይ ኢትዮጵያውያኑን ያሰባስባል። በፍራንክፈርቱ ዝግጅት በአውሮፓ የሚኖሩ እስከ 25 ሺህ ኢትዮጵያውያን እንደሚታደሙ ይጠበቃል። ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰበሰባቸው ኢትዮጵያውያን ስለዝግጅቱ ሲወያዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ አውሮፓ መምጣት በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል። እነሱም በለንደንና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትየጵያውያንን በማሰባሰብ ወደ ፍራንክፈርት ለመትመም በመሰናዳት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ከዶክተር ዐቢይ ጋር ለመምከር መዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት። ኢትዮጵያን በልባቸው አትመዋት በመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ሀገርን የመገንባት ጥሪን ያነገበው የውጭ ጉዞ መነሻውን ኢትዮጵያ መዳረሻውን አውሮፓ ሊያደርግ ቀናት ቀርተውታል።