የመንግስት ተቋማት በጥናት ላይ የተመሰረተ የለውጥ መሳሪያዎችን ቢተገብሩ ውጤታማ ይሆናሉ..የዘርፉ ባለሞያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ተቋማት በጥናት ላይ የተመሰረተ የለውጥ መሳሪያዎችን ቢተገብሩ ውጤታማ ይሆናሉ..የዘርፉ ባለሞያዎች
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 የመንግስት መስሪያ ቤቶች የአሰራር ማሻሻያዎችንና የለውጥ መሳሪያዎችን በጥናት ላይ ተመስርተው ተግባራዊ ካደረጉ ውጤታማ እንደሚሆኑ የሥራ አመራር አማካሪ ባለሙያዎች ገለጹ። ቀደም ሲል መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ (ቢ ፒ አር)፣ የውጤት ተኮር ስራ ምዘና (ቢ ኤስ ሲ)፣ ካይዘን የአመራር ፍልስፍናና የዜጎች ቻርተር በበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሲተገበሩ ቆይተዋል። እስከ አሁን በነበረው ሁኔታ መንግስት የለውጥ መሳሪያዎቹን በሁሉም ተቋማት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ግን የለውጥ መሳሪያዎቹ የተቋማቱን የሥራ ባህርይ ያገናዘበ ባለመሆናቸው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። የስራ አመራር ልማት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ አቀና ኢዮብ እንደሚሉት ቀደም ሲል በነበረው አሰራር የመንግስት ተቋማት የለውጥ መሳሪያዎችን በፍላጎታቸው ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ውጤታማነቱ ላይ ውስንነት ታይቷል። በአሁኑ ወቅት ተቋማት በራሳቸው ፍላጎት ስራን ለማቀላጠፍ የለውጥ መሳሪያዎችን በጥናት ላይ ተመስርተው ተግባራዊ ካደረጉ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉም ጠቁመዋል። የስልጠና፣ የምክርና የምርምር አማካሪ አቶ ዳንኤል ዘውዴ በበኩላቸው ተቋማቱ የሚስማማቸውን የለውጥ መሳሪያ ተግባራዊ ሲያደርጉ ጥቅምና ጉዳት እንዳለው ይገልጻሉ። ተቋማት እንደ ሥራ ባህሪያቸውና እንደተሰጣቸው ተልዕኮ የለውጥ መሳሪያዎችን በራሳቸው መንገድ በመተግበር ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል የተቀናጀ አገራዊ ለውጥ በማምጣት በኩል ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ በበኩላቸው ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው ተቋማት ተመሳሳይ አሰራር ቢከተሉ ስጋቱ እንደሚቀንስ አመላክተዋል። አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ተቋማት ከሌሎች በባህሪ ከማይመስሏቸው ተቋማት ጋር ተመሳሳይ የለውጥ መሳሪያ መተግበር የማይጠበቅባቸው እንደሆነም ተናግረዋል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች የአሰራር ማሻሻያዎችን በራሳቸው መንገድ ተግባራዊ ማድረጋቸው ብቻ ለውጤታማነት ዋስትና ሊሆን እንደማይችል የጠቆሙት ዶክተር ታከለ ውጤታማ የሆነ የአሰራር ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ በተቋማቱ የፈጠራ አቅም ላይ እንደሚወሰንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በነባሩ አሰራር ተቋማት የለውጥ መሳሪያዎች በሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ሚኒስቴር በኩል ሲዘጋጅላቸው የነበረ ሲሆን መንግስት በቅርቡ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ላይ ባደረገው ማሻሻያ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በኮሙሺንነት በመደራጀቱ ተቋማት በራሳቸው የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ።