ቀጥታ፡

መንግሥት ለሸቀጥ ዋጋ መናር ምክንያት በሆኑ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

አዳማ ጥቅምት 13/2011 ለሸቀጥ ዋጋ መናር ምክንያት በሆኑ ደላሎች፣ ዋጋን በምክር የሚወስኑ አድመኛ ነጋዴዎችና ያልተገባ ጥቅም ለማድበስበስ ሲሉ በሚተባበሯቸው የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጠየቀ። ተቋሙ የሸቀጦች ዋጋ መናር በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማመላከት ያካሄደውን ጥናት መሠረት በማድረግ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ግኝቶችን በባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል። የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ሠራዊት ስለሺ በዐውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን በያዘበት ሁኔታ ነፃና ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ተግባራዊ ማድረግ የማይታሰብ ነው። በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በንግድ ሂደቱ ላይ ህገወጥ ድርጅቶች ሲስተዋሉ ይታያል ያሉት ወይዘሮ ሠራዊት፣ ድርጊቱ ሸማቹን        ኅብረተሰብ ሊቋቋመው ወደማይችለው የኑሮ ውድነት እየተገፋ ነው ብለዋል። መንግሥት አሁን እየታየ ያለውን የገበያ ዋጋ መናር ለማስተካከል በደላሎች፣ የገበያ ዋጋን በምክር በሚወስኑ አድመኛ ነጋዴዎችና ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ በሚተባበሯቸው የመንግሥት አካላት ላይ ውሎ ሳያድር ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድም አሳስበዋል። የጥናቱ ግኝቶች በመድረኩ ላይ ይፋ ያደረጉት የተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ እንደገለጹት ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የንግድ ውድድርና የሸማቶች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን፣ የፌዴራል ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ያካተተ ነው። ጥናቱ የሥራ ኃላፊዎችን፣ ሠራተኞችን ነጋዴዎችንና ሸማቶችን ጨምሮ 1ሺህ 98 ሰዎች በመጠየቅና በውይይት አሳትፏል። ከጥናቱ ግኝቶች መካከል የአቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆንና ኅብረተሰቡ በተሻለ ዋጋ አማራጭ ምርት በብዛት አለማግኘት፣ የአገር ውስጥ ፍላጎት ሳይሟላ ወደ ውጭ እንዲላክ በማድረግ በምርት አቅርቦት ላይ እጥረት እንዲፈጠርና የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል የሚል ይገኝበታል። የግብርና ውጤቶች የምግብ እህሎች በኮንትሮባንድ መልክ እንዲወጡ በመደረጉ በገበያው ላይ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉ አንዱ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል። የሸማቶች ኅብረት ስራ ማህበራት አመራሮች የተረከቡትን ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚው ከማዳረስ ይልቅ የተወሰነውን ካከፋፈሉ በኋላ ቀሪውን አየር በአየር ለሚነግዱ ህገ ወጥ ሰዎች የሚሸጡበት አጋጣሚ መኖሩንም በጥናቱ ተጠቁሟል። የሸማቶች ኅብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለታለመለት ዓላማ ከማዋል ይልቅ ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው ሱቅ ከፍተው ዘይትና ስኳር እንዲቸረችሩ የሚያደርጉ ግለሰቦች መኖራቸውንም በጥናቱ ላይ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። መንግሥት ያደረገው የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ 15 በመቶ ሆኖ እያለ አብዛኛዎቹ ጭማሪዎች ግን ከ30 እስከ 50 በመቶ መድረሳቸው በጥናቱ ግኝት ውስጥ ተካቷል። የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ በተደረገ ማግስት ከውጭ ምንዛሪው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው የአገር ውስጥ ምርቶችና ሸቀጦች በተለይም የግብርና ምርቶች ላይ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት አጋጣሚ አለ ተብሏል። እነዚህና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ሥራ ለኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የተበተበ በመሆኑ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። የንግድ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች ከነጋዴዎች ጋር በጥቅማ ጥቅም በመተሳሰር ኃላፊነትን አለመወጣትና ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ በሕጉ መሠረት ያለመከታተል ጥናቱን በችግርነት ካስቀመጣቸው ነጥቦች አንዱ ነው። ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በቡድን ተደራጅተው በቡድን በሚወስኑ አድመኞች ላይ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ገበያውን እየጎዳው ነው ተብሏል። ገበያውን ገዢና ሻጭ የሚወስኑት ሳይሆን፣ ደላሎች እጃቸውን በስፋት በማስገባት እየበጠበጡ ነው ተብሏል። ስለዚህ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ገበያውን ለማረጋጋት ሲባል በህገ ወጦች ላይ እርምጃ እንዲወስድና ህብረተሰቡም የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት ህጋዊ፤ ነፃና ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥናት ገምቢ ሚና እንዲጫወት ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል። በአውደ ጥናቱ ላይ ለነፃ ገበያ ስርዓት የግብይት ሂደት ላይ በቀጥታም ይሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም