ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ14ኛው ዙር 'ይቀበሉ! ይሸለሙ!' የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ እጣ ወጣ

አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ14ኛው ዙር 'ይቀበሉ!ይሸለሙ!' የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ እጣ ለባለ ዕድለኞች ወጣ። በዚሁ ወቅት የባንኩ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሌን ኃይሉ እንዳሉት፤ የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብር በማገዝ ሃብት አፍርቶ በአገሪቱ ልማት ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል ባንኩ ስትራተጂያዊ ትኩረቱ አድርጎ እየሰራበት ይገኛል። "የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል እንዲዳብር እና ባንካችን የውጭ ምንዛሬ መቀበያና መመንዘሪያ ትክክለኛ ቦታ አድርጎ እንዲቀበል የተለያዩ የማበረታቻ ፕሮግራሞች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል" ብለዋል። ከነሀሴ 10 ቀን 2010 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም የቆየው የ14ኛው ዙር 'ይቀበሉ! ይሸለሙ!' የውጭ ማበረታቻ መርሃ ግብር 83 ሽልማቶች ለእጣ አሸናፊዎች ተዘጋጅቷል። በዚህም መሰረት 1ኛ ዕጣ የቤት አውቶሞቢል፣ 2ኛ ዕጣ 2 ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች፣ 3ኛ ዕጣ 16 ቴሌቪዥኖች፣ 4ኛ ዕጣ 64 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች ለባለዕድለኞች በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ ወጥቷል። ባንኩ በመላው ዓለም ከሚገኙ ከ720 በላይ ባንኮች ጋር በመረጃ መገናኘቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም