ቀጥታ፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጾ እውቅና ተሰጣቸው

አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መጎልበት ላበረከቱት አስተዋጾ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽልማትና እውቅና ተበረከተላቸው። የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አቶ ኃይለማርያም አገሪቱን በመሩበት የሃላፊነት ዘመናቸው በአገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መጎልበት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲጎለብት የሚያስችሉ ኢንስቲትዩቶች በስልጣን ዘመናቸው እንዲቋቋሙ ማድረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል። አቶ ኃይለማርያም ስልጣንን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ስልጣን ከለቀቁም በኋላ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ መኖር እንደሚቻል ያሳዩ መሪ መሆናቸውን ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ተናግረዋል። በዚህ ተግባራቸው ዕውቅናና ሽልማት ማበርከቱን ገልጸው፤ በቀጣይም ተቋሙ ከአቶ ኃይለማርያም ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ገልጸዋል። አቶ ኃይለማርያም በበኩላቸው ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በኢትዮጵያ ሳይንስ፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ እንዲጎለብት የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም