በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አምስት ተጫዋቾች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሻረ - ኢዜአ አማርኛ
በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አምስት ተጫዋቾች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሻረ
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አምስት ተጫዋቾች ላይ ተጥሎ የነበረውን የእገዳና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ሻረ። ሚያዚያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ የፌዴራል የመሐል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ በመደብደቡ ምክንያት ጨዋታው መቋረጡ ይታወሳል። ጉዳዩን ሲያጠራ የነበረው የፌዴሬሽኑ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ማንኛውም ውድድሮች የእድሜ ልክ እንዲታገዱ፤ በተጨማሪም የወልዋሎ ተጫዋቾች በረከት አማረ፣ አለምነህ ግርማ፣ አሳሪ አልማህዲ፣ ማናዬ ፋንቱ፣ በረከት ተሰማ እና አፈወርቅ ኃይሉ ለስድስት ወራት እንዲታገዱ እንዲሁም እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር እንዲቀጡ፤ ሌላው የወልዋሎ ተጫዋች ዋለልኝ ገብሬ የሁለት ዓመት እገዳ እና የ15 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈበትና ወልዋሎ በጨዋታው የፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆንና 250 ሺህ ብር እንዲከፍል፤ እንዲሁም የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል አሰልጣኝ አቶ ሃብቶም ኪሮስና የክለቡ ወጌሻ አቶ ቢንያም ተፈሪ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ወስኖ ነበር። የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቅጣቱን አስመልክቶ ባቀረበው ይግባኝ መሰረት የፌዴሬሽኑ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ተመልክቶ በስነ-ምግባር ኮሚቴ የተወሰኑ ቅጣቶችን መርምሮ ትናንት ማምሻውን ማስተካከያ አድርጓል። በዚህም መሰረት በረከት ተሰማ፣ አለምነህ ግርማ፣ ማናዬ ፋንቱና አፈወርቅ ኃይሉ በኮሚሽነሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ ዳኛ ከበዋል የሚል እንጂ ዳኛውን ደብድበዋል የሚል ባለመሆኑና በሰው፣ በሰነድና በተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ በመታገዝ በተደረገ ማጣራት አራቱ ተጫዋቾች ተጥሎባቸው የነበረው የስድስት ወር እገዳና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተነስቶላቸዋል። አራቱ ተጫዋቾች ዳኛን በመክበብ በፈጸሙት ጥፋት የከባድ የጽሁፍ ማስጠንቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል። ሌላኛው ተጫዋች ዋለልኝ ገብሬ በኮሚሽነሩ በቀረበው ሪፖርት ዳኛ ደብድቧል በሚል የቀረበው መረጃ በዕለቱ ጨዋታውን የመሩት ዳኞች የቃል ምስክርነት ጋር እርስ በእርስ የሚጣረስ በመሆኑና በተንቀሳቀሽ ምስል ማስረጃው ተጫዋቹ ዳኛ አለመማታቱ በመረጋገጡ የዋለልኝ ገብሬን የሁለት ዓመት እገዳ እና የ15 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሻር ወስኗል። ዋለልኝ ገብሬ ዳኛውን በመክበብ ግርግር ውስጥ በመሳተፉና ያለፈቃድ ከተቀያሪ ወንበር ላይ ተነስቶ ወደ ሜዳ በመግባቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰውና አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል ሲል የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ወስኗል። በኮሚሽነሩ ሪፖርት ዳኛ መማታቱ የተረጋገጠው የወልዋሎ ተጫዋች አሳሪ አልመሐዲ የስነ-ምግባር ኮሚቴው የጣለበት ቅጣት ከፈጸመው ተግባር አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ የስድስት ወራት እገዳና የ10 ሺህ ቅጣት ወደ አንድ ዓመት እገዳና 20 ሺህ ብር ቅጣት ጨምሯል። የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ለስድስት ወራት ከማንኛውም የስፖርት ውድድሮች እገዳና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ጸንቷል። ፌዴራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴን የደበደበው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ማንኛውም ውድድሮች የእድሜ ልክ እገዳ ውሳኔ እንዲጸና ተደርጓል። የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ክለቡ እንዲከፍል ተብሎ በስነ-ምግባር ኮሚቴው የተወሰነውን ውሳኔ ቡድን መሪው ላጠፋው ጥፋት ክለቡ የገንዘብ ቅጣቱን ይክፈል የሚለው ውሳኔ አግባብ ባለመሆኑ የወልዋሎ አዲግራት አቶ ማሩ ገንዘቡን እንዲከፍሉ ሲል ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ወስኗል። የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በጨዋታው የፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆንና 250 ሺህ ብር እንዲከፍል የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ እንዲጸና ተደርጓል። በተጨማሪም የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል አሰልጣኝ አቶ ሃብቶም ኪሮስና የክለቡ ወጌሻ አቶ ቢንያም ተፈሪ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ውሳኔን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አጽንቶታል። ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ውሳኔውን ያስተላለፈው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስነ-ምግባር መመሪያ፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ህጎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አስታውቋል። በተወሰኑት ውሳኔዎች ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በኋላ ቅሬታ ካለው ለዓለም አቀፉ የስፖርት ጉዳዮች ፍርድ ቤት (ካስ) ማቅረብ እንደሚችልም ገልጿል።