የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር በትምህርት ጥራት ላይ የጀመኩትን ስራ አጠናክሬ እቀጥላለሁ- የወላይታ ልማት ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር በትምህርት ጥራት ላይ የጀመኩትን ስራ አጠናክሬ እቀጥላለሁ- የወላይታ ልማት ማህበር
ሶዶ ጥቅምት 12/2011 የወላይታ ልማት ማህበር የተማረ የሰው ኃይል በመፍጠር በትምህርት ጥራት ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡ ልማት ማህበሩ የሚያስተዳድረው የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለሚገቡ 65 ተማሪዎች አሸኛኘት አድርጓል፡፡ የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት የወላይታ ልማት ማህበር በምግብ ዋስትና፣ በጤናና በትምህርት ስራዎችን በመስራት የወላይታን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ በእውቀት የዳበረና ራዕይ ያለው የተማረ የሰው ሃይል በመፍጠር የትምህርት ጥራት ላይ የጀመረውን ስራም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚና በመልካም ስብዕና የተገነቡ ተማሪዎችን በማፍራት ረገድ ልማት ማህበሩ የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤቱን ተሞክሮና ልምድ በማስፋት በዞኑ የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን የመደገፍና የማብቃት ተግባር እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ጎኣ በዘንድሮ ዓመት 65 የሚሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 65ቱም ተማሪዎች የወሰዱትን ፈተና በጥሩ ውጤት ማለፋቸውን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ዘጠኝ ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት በማስመዝገብ በአገር አቀፍ ደረጃ መሸለማቸውንም አስታውሰዋል፡፡ የ10ኛ ክፍል ፈተና የተፈተኑት 59 ተማሪዎች አራት ነጥብ ማምጣታቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናም ተፈታኝ ተማሪዎች በክልሉ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ መምህራን፣ ወላጆች፣ የትምህርት ቤቱና የማህበሩ ሰራተኞች የሚያሳዩት ቁርጠኝነትና የኃላፊነት ስሜት ለትምህርት ቤቱ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትርንጎ ዋድሎ እንደተናገሩት ማህበሩ ለትምህርት ጥራት በሰጠው ትኩረት የሊቃ ትምህርት ቤት በየዓመቱ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ ለልጆቹ ውጤታማነት የወላጅ ድጋፍ መለየት የለበትም ያሉት ወይዘሮ ትርንጎ ትምህርት ቤቱ ልጆችን በስነ ምግባር ማነጹ ለውጤታማነቱ የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተናን የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ተማሪ አበባየሁ አየለ እንዳለው ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በርትቶ በማጥናቱ ለስኬት መብቃቱን ገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል መመደቡን የተናገረው ተማሪ አበባየሁ በቆይታውም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በርትቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ባለፉት አስር ዓመታት ከ430 በላይ ተማሪዎችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና እንዲወስዱ በማድረግ ሁሉም ተማሪዎች የተሰጠውን ፈተና እንዲያልፉ ማድረጉን ከትምህርት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡