ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ክትትል እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ክትትል እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 የዜጎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑን በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ቆንስላ ጄነራል አብዱ ያሲን በጅዳ በሚገኙ እስር ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን መጎብኘታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያውያንን ሰብአዊ መብት በማስከበር ያሉበትን ሁኔታ መከታተል የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ዋነኛ ተግባር እንደሆነ ተገልጿል። ቆንስላ ጄነራሉ በዳህባን እና ሺሜሲ የተባሉ ማረሚያ ቤቶች በመጎብኘት በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው የሚገኙ ዜጎች አያያዝና የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ታራሚዎች ሊፈቱ በሚችሉበት ዙሪያ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ጋር ተወያይተዋል። እንዲሁም ከታራሚዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ጽህፈት ቤቱ አስፈላጊውን ክትትልና በሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግና ከጎናቸው እንደሚሆን ገልጸዋል። የዜጎችን ሰብአዊ መብት ከማስጠበቅ አኳያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ አስፈላጊውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ክትትል እንደሚያደርግ መናገራቸውን የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።