ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሴቶች ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሴቶች ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠየቁ
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሴቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጥሪ አቀረቡ። የሴቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት ዓላማው ያደረገ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል። የመዲናዋ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀው በዚሁ ጉባኤ ላይ ከየክፍለ ከተማው ከሚገኙ ወረዳዎች የተጋበዙ የተለያዩ ሴት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል። በጉባኤው ላይ ልጆች ይዘው ለዓመታት ላስቲክ ወጥረው ህይወታቸውን በችግር የሚገፉ ሴቶች፣ ሴቶችን በአግባቡ አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት፣ አካል ጉዳተኞችን ተሳቢ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በሚጠበቀው ልክ አለመተግበራቸው ከተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሃሳቦች ናቸው። የትራንስፖርት ችግርም የከተማው ነዋሪ ፈተና እንደሆነ ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ሴቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ዝግጁ ነው። እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ እንዲቀርብ የጠየቁት ምክትል ከንቲባው ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ አመራርነት የመጡበት የአሁኑን ወቅት ዕድል በመጠቀም ለለውጥ መትጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ''ሴቶች የለውጡ አካል ስለሆናችሁ ለውጡን ደግሞ አንድ ላይ ተጋግዘን ከመራን፤ ወደ ኋላ የሚመመልሰን የትኛውም ኃይል የለም'' ብለዋል። ''እናንተ ካገዛችሁን ከመከራችሁን ለሁላችንም የምትሆን የተሻለች ከተማን እውን ማድረግ እንችላለን'' በማለት ጥሪ አቅርበዋል። የየካ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምጸሀይ ጳውሎስ በበኩላቸው ለውጡን ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሴቶችን ህገ ወጥነትን መከላከል ላይ ማተኮር እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። ''ያለ ሴቶች ተሳትፎ የትኛውም አይነት ልማት፤ የትኛውም አይነት ኦኮኖሚ ወደፊት ሊሄድ አይችልም'' ያሉት ወይዘሮ ዓለምጸሀይ ለውጡን ከማስቀጠል ጎን ለጎን የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። በዕለቱ ለምክትል ከንቲባ እንጂር ታከለ ኡማ በከተማዋ እየሰሩ ላሉት ስራ እውቅና የሚሰጥ የፎቶ ሽልማት ተበርክቷል።