ወላይታ ድቻና ደቡብ ፖሊስ አንድ አቻ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻና ደቡብ ፖሊስ አንድ አቻ ተለያዩ
ሶዶ ጥቅምት 12/2011 ወላይታ ድቻና ደቡብ ፖሊስ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያዩ፡፡ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲዬም ትናንት በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው የደቡብ ፖሊስ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ በመጀመሪያው ዙር የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአራተኛው ደቂቃ ላይ በ94 ቁጥሩ በልዑል ስምኦን በኩል የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ተጋጣሚው በ48ኛው ደቂቃ በሦስት ቁጥር ለባሹ አንዷለም ንጉሴ አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል፡፡ የወላይታ ድቻ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ከጨዋታው በኋላ እንደገለጹት ጨዋታው ክለቡ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከመጀመሩ በፊት የተደረገ የመጨረሻው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአግባቡ እንዳልተንቀሳቀሱ የተናገሩት አሰልጣኝ ዘነበ፣ ጨዋታው ክፍተቶቻቸውን ለመድፈን እንዳገዛቸው አመልክተዋል። የደቡብ ፖሊስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸዉ "አዲስ መጪ ሆነን ከወላይታ ድቻ ጋር በሜዳው አቻ መውጣት መቻላችን የቡድናችንን ስነ ልቡና ከመገንባት አንጻር ፋይዳው የላቀ ነው'' ብለዋል፡፡ ደቡብ ፖሊስ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተወዳድሮ በዚህ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ያደገ ክለብ ነው። የወላይታ ድቻ ክለብ ደግሞ በአምናው በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ካደረጋቸው ጨዋታዎች 33 ነጥብ በመያዝ በውድድሩ ዘጠነኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡