ቀጥታ፡

የመኾኒና አላማጣ ከተሞች ምሩቃን ወጣቶች ከሥራ ፈላጊነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገሩ ነው

ማይጨው ጥቅምት 12/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን መኾኒና አላማጣ ከተሞች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ወጣቶች ከሥራ ፈላጊነት ወደ  አምራችነት በመሸጋገር ላይ ናቸው ። ወጣቶቹ በማህበራት ተሰባስበው ያመረቱትን ወደ ገበያ በማቅረብም ሕይወታቸውን መምራት ጀምረዋል። በራያ ዓዘቦ ወረዳ መኾኒ ከተማ የመካኒካል ምህንድስና ዘርፍ ተመራቂዎች "ቃል" በሚል የሰየሙትን ማህበር በመመስረት ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች መካከል ናቸው፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ጉኡሽ ጎሸሽ እንዳገለጸው ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ባገኙት 400 ሺህ ብር በመጠቀም በቀን 110 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቴራዞ  በማምረት ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ላይ ናቸው። የማህበሩ አባላት ከሽያጭ ከሚያገኙት ገንዘብ  በነብሰወከፍ አንድ ሺህ ብር ለኑሮ መደጎሚያ እንደሚወስዱ ሊቀመንበሩ ገልጿል፡፡ ''ኅብረተሰቡ ምርቱን እየለመደው ሲሄድ የተሻለ ገቢ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን'' በማለትም ተስፋቸውን ይገልጻሉ። ሌላው በኬሚካል ምህንድስና ዘርፍ የተመረቁ ሦስት ጓደኟሞች ተደራጅተው ያቋቋሙት የልብስ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ ነው። ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም 240ሺህ ብር በመውሰድ "ሉሲ" የልብስ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና ማቋቋማቸውን የሚገልጸው ደግሞ የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ሓለፎም ኃይለ ነው፡፡ ማህበሩ በቀን 2ሺህ 400 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና በማምረት ከአካባቢያቸው ገበያ አልፈው አፋር ክልል ማከፋፈል ጀምሯል፡፡ "አውዛ" የጠመኔ ማምረቻ ኢንተርፕራይዝን በማቋቋም የጠመኔ ምርቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኑን የሚገልጸው ደግሞ የአላማጣ ከተማ ነዋሪና የመካኒካል ምህንድስና ምሩቅ ወጣት ሰመረ ዕቁባይ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው 314 ሺህ ብር ብድር ወስዶ ያቋቋመው ኢንተርፕራይዝ  በቀን 200 ሺህ ጠመኔ በማምረት ለትምህርት ቤቶች እያቀረበ መሆኑን ይገልጻል። በየወሩ ከሚያገኘው 15ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ  በማግኘት ሕይወቱን ለመምራት አስችሎኛል ይላል። በተጨማሪ ለ23 ሠራተኞችም ሥራ መፍጠሩን ሰመረ ይናገራል፡፡ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ባመቻቸለት የገበያ ትስስር የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ የመስሪያ ቦታ በነጻ በመስጠት ድጋፍ እንዳደረጉለትም ገልጿል፡፡ የመኾኒ ከተማ  ማንፋክቸርንግ ልማት ጽህፈት ቤት የገበያ ትስስርና ፕሮሞሽን ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ጥጋቡ ጽህፈት ቤታቸው በማምረቻ ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ ወጣቶች ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። በተለይም በቴራዞና በፈሳሽ ሳሙና ምርት ለተሰማሩት ወጣቶች  የማምረቻ ቦታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በክልል ደረጃ በሚካሄዱ ኤግዚቢሽን የቴራዞና ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም