ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ለማንሳት ነገ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ለማንሳት ነገ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማ አባ ጅፋርና የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊው መከላከያ እግር ኳስ ክለብ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳት ነገ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ጨዋታው በባለፈው ዓመት መጨረሻ መከናወን ይገባው የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቶ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በመጠናቀቁ ምክንያት ጨዋታው በዚህ ዓመት እንዲካሄድ ግድ ብሏል። ሁለቱ ክለቦች ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው 13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ተገናኝተው በመደበኛ 90 ደቂቃ ሁለት እኩል ተለያይተው ወደ መለያ ምት ያመሩ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር 4 ለ 3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ክለቦች በነበራቸው ግንኙነት ጅማ አባ ጅፋር አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ መውጣታቸው የሚታወስ ነው። መከላከያ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛውን ዋንጫ ለማንሳት ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመቱን በዋንጫ ለመጀመር የሚያደርጉት ፍልሚያ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ ይጠበቃል። የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የሚያነሳው ክለብ ለ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያደርገውን ውድድር በጥሩ መነሳሳት ለመጀመር ያስችለዋል ተብሎ ይታመናል። አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን አሸንፎ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው። በ1977 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ 26 ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 5፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላሉ።