ቀጥታ፡

በአቢዬ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ውጤታማ የሰላም ማስከበር ሥራ ማከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 12/2011 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሰላም አስከባሪ  በአብዬ የተሰማራው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ። በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሽፈራው ጃርሶ የሰላም አስከባሪውን አባላት አቢዬ ሄደው ማነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መረጃ አስታውቋል። አምባሳደር ሽፈራው ሰራዊቱ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በጥሩ ዲሲፕሊን ተግባሩን በማከናወን በአካባቢው ለመጣው ለውጥና ለአገራችን በጎ ገጽታ መገንባት ለተጫወተው ሚና ያላቸውን አድናቆትና ምስጋናቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ከሚያዋጡ ጥቂት አገሮች መካከል ቀዳሚ ስፍራ ላይ የምትገኝ መሆኑዋንም ጠቅሰዋል። የሰላም አስከባሪው ልዩ ልዩ ክፍሎች አባላት ለአምባሳደሩ በሰጡት ማብራሪያ አጠቃላይ የሰራዊቱን አደረጃጀት፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር ያስገኘውን አበረታች ውጤት፣ ለህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ገልጸው፣ በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም መፈጠሩና ከቀያቸው ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ መመለስቸውንም አስረድተዋል። ሰራዊቱ ለአካባቢው ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝና በተለይ የሰራዊቱ ሴት አባላት በአገራችን የተከበረውን የአሸንዳ በዓል ምክንያት በማድረግ ባዘጋጁት ፕሮግራም ገቢ በማሰባሰብ በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸውላቸዋል። በተያየዘም በአቢዬ የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ የፀጥታ ኃይል (UNISFA) አባላት ላበረከቱት ውጤታማ የሰላም ማስከበር ሥራ የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ አምባሳደር ሽፈራው ተገኝተው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል። ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የሰላም ማስከበር ልምድ ያላት መሆኑን አስታውሰው ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር የምታሳየው ቁርጠኝነት የሚመነጨው ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ መሆኑን መግለጻቸውንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ሱዳን የሚወዛገቡበት የአቢዬን ድንበር ችግር ለመፍታት እ.አ.አ በ2011 በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ወታደሮቻቸው ድንበሩን ለቀው በመውጣት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቦታውን እንዲቆጣጠር መስማማታቸው የሚታወስ ነው። ከመንግስታቱ ድርጅት ውሳኔ በኋላ በተመሳሳይ እ.አ.አ በ2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሶስተኛ ወገን  የጸጥታ ሃይል ቦታውን እንዲቆጣጣር የውሳኔ ሃሳብ ማስተላለፉም ይታወሳል። በዚሁ መሰረት በኢቢዬ የተባበሩት መንግስታት ጊዚያዊ የፀጥታ ኃይል (UNISFA) የተቋቋመ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮቹን በማሰማራት በቦታው ከሚኖሩ ዜጎች ጋር በመሆን ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም