በቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አስቀድሞ ማምከን የሚያስችል አሰራር መቀየስ ይገባል-አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
በቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አስቀድሞ ማምከን የሚያስችል አሰራር መቀየስ ይገባል-አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 በቤተ-ክርስቲያንና በአገልጋዮች ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አስቀድሞ ማምከን የሚያስችል አሰራር መቀየስ አስፈላጊ ነው ሲሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። በኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ዛሬ በፓትሪያክ ጽህፈት ቤት ተካሂዷል። በመክፈቻው ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ-ኢትዮጵያ እንዳሉት በየአካባቢው ጠንካራ የግንኙነት መረብ በመዘርጋትና ከፍትህና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። በዚህም በቤተ-ክርስቲያንና በአገልጋዮች ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አስቀድሞ ማምከን የሚቻልበት አሰራር መቀየስ እንደሚያስችል ነው የገለጹት። የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዋና ዓላማ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመቋቋም፣ ለምዕመናን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማበርከት መሆኑንም ገልጸዋል። በሰው ልጆች መካከል እኩልነት፣ ሰብዓዊነትና ፍትህ እንዲሰፍን ቤተ-ክርስቲያኗ የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረግ እንድትችል መሆኑንም ተናግረዋል። የዘንድሮውን ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው "ቤተ-ክርስቲያኗ ሐዋሪያዊ ተልዕኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቀፋት ሆኖ የቆየው የሲኖዶሶች መለያየት ተወግዶ አንድነታቸው እውን የሆነበት መሆኑ ነው" ብለዋል። በሌላ በኩል ከዚህ በተቃራኒ "ቤተክርስቲያን በከፋ መልኩ የተደፈረችበት፣ ካህናትና ምዕመናን በአሰቃቂ ጭካኔ የሰማዕትነት ጽዋ የተቀበሉበት ማግስት ነው" ሲሉም ተናግረዋል። በቅርቡም በኢትዮጵያ ሶማሌ አገረ ስብከት የተፈጸመው ግፍ፣ እልቂትና ውድመት ቤተ-ክርስቲያኗን ክፍኛ የተደፈረችበት ነው ብለዋል። በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንዲቆሙና ለካህናትና ምዕመናን አስተማማኝ መፍትሄ አበጅቶ ዘላቂ ዋስትና እንዲኖር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የመልካም አሰተዳደር እጦት፣ የሀብት አያያዝ ክፍተት፣ የምዕመናን ፍልሰት፣ ከቤተ-ክርስቲያን መዋቅር ውጭ በግላቸው አስተዳደራዊ መዋቅር እየዘረጉ ያሉ ማህበራትን በደንብና በመመሪያ መልክ ማስያዝ ጊዜ የማይሰጣቸው ችግሮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ጉባኤው ሁሉንም የቤተ-ክርስቲያን ስራዎች ያካተተ፣ ጥልቅና ችግር ፈቺ የሆነ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል መሪ እቅድ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ መንገዶች ላይ መውያያት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል። ይህም የቤተ-ክርስቲያንን አሰራር ዘመናዊና ግልጽነት ያለው ለማድረግ እንደሚረዳ አክለዋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በብሩህ ተስፋና በስጋት መንታ መንገድ ላይ መቆሟን ገልጸው ስጋቱ ተወግዶ ብሩህ ተስፋው ብቻ እንዲፈነጥቅ የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጋር በትብብር ለመስራት ቅዱስ ሲኖዶስ ዝግጁነቱን መግለጽና የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም መስራት ይገባልም ብለዋል። ጉባኤው የተጠቀሱ አንገብጋቢና አገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት መርምሮ አገሪቱንና ቤተ-ክርስቲያኗን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ ፓትሪያርኩ አሳስበዋል።