ቀጥታ፡

ሊዲያ ታፈሰ በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድር ለዳኝነት ተመረጠች

አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በህዳር 2011 ዓ.ም በጋና በሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድር በዳኝነት እንድታጫውት ተመረጠች። ውድድሩ ከህዳር 8 እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገሪቱ ርዕሰ-መዲና አክራ እና ኬፕኮስት ከተሞች ይካሄዳል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ በውድድሩ የሚያጫውቱትን 16 ዋና እና 16 ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኞች ትናንት ሲያሳውቅ ኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል ዳኝነት እንድታጫውት መርጧታል። ሊዲያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 ካሜሩን ባስተናገደችው 10ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ያጫወተች ሲሆን በወቅቱ አዘጋጇ ካሜሮንና ግብጽ ያደረጉትን የመክፈቻ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት መምራቷ የሚታወስ ነው። በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ለዘጠነኛ ጊዜ በተካሄደው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ሁለት ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት መምራቷ አይዘነጋም። በተያያዘ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ትናንት በጋና አክራ የ11ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የምድብ ድልድልን ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት በምድብ አንድ አዘጋጇ ጋና፣ ማሊ፣ አልጄሪያና ካሜሮን ሲደለደሉ በምድብ ሁለት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያና ኬንያ ተመድበዋል። ውድድሩ ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም በአክራ ስፖርት ስታዲየም አዘጋጇ ጋና ከአልጄሪያ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል። የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በጋና የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ በቅድመ ማጣሪያው ሊቢያን በማሸነፍ በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ከአልጄሪያ ጋር በማድረግ በድምር ውጤት በመሸነፉ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልቻለም። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሉሲዎቹ ከአልጄሪያ ጋር በተደረገው ጨዋታ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጥምር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ አሰልፋለች የሚል ክስ ለካፍ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ካፍ ጉዳዩን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ኢኳቶሪያል ጊኒ ለውድድሩ አልፋ የነበረ ቢሆንም በተጫዋች ተገቢነት ክስ ካፍ አግዷት በምትኳ ኬንያ ማለፏ ይታወቃል። ናይጄሪያ የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫን ስምንት ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ስትይዝ ቀሪውን ሁለት ዋንጫ ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸንፋለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም