ቀጥታ፡

ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና በመጪው ሐሙስ ይጀመራል

አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011 ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና በመጪው ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ይጀመራል። ለሁሉም ክፍት በሆነው ሻምፒዮና በወንዶች ከ 52 እስከ 80 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ46 እስከ 67 ኪሎ ግራም በአጠቃላይ በ12 ኪሎ ምድብ 100 ተወዳዳሪያዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድሩ ዓላማ በአገር አቀፍ ውድድሮች ዕድል ያላገኙ ወጣት ስፖርተኞች እንዲሳተፉ ማድረግ ነው። ተወዳዳሪዎቹ በስፖርቱ ያላቸውን አቅም ለማጎልበትና ልምድ እንዲቀስሙ ከማድረግ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለመላው አፍሪካ ውድድር ብቁ ስፖርተኞች ከውድድሩ እንደሚመለመሉ ጠቁመዋል። ውድድሩ ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ በክልልና በከተማ አስተዳድሮች ለሚገኙ የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽኖች ጥሪ መቅረቡን አመልክተዋል። በአጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊዎች ከሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ በሁሉም የክብደት ዘርፍ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከትል የ10፣ 5ና 3 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ጠቁመዋል። በሁለቱም ጾታ ምርጥ ስፖርተኛ ተብለው ለሚመረጡ ተወዳዳሪዎች የ5 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጥና በሁለቱም ጾታ አዲስ ለሚታዩ ወጣት ተፋላሚዎች የ5 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከት አቶ ዳዊት አስረድተዋል። በተያዘው ዓመት መሰል ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በየውድድሩ የተሳትፎ ነጥብ በመመዝገብ በዓመቱ መጨረሻ ለአጠቃላይ አሸናፊዎች ከፍተኛ ሽልማት እንደሚበረከት ጠቅሰዋል። ውድድሩ እስከ ጥቅምት 19  ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል፡፡ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአህጉር ደረጃ ውጤት በማምጣት የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት ላይ ይገኛል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም