ቀጥታ፡

የታዳጊ ወጣቶች የቮሊቦል ፕሮጀክት መርሃ ግብር ውጤታማ አይደለም

አዲስ አበባ  ጥቅምት 10/2011 የታዳጊ ወጣቶች የቮሊቦል ፕሮጀክት መርሃ ግብር ውጤት አላስገኘም ተባለ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን 19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በጠቅላላ ጉባኤው የታዳጊ ወጣቶች የቮሊቦል ፕሮጀክት መርሃ ግብርን የተመለከተ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። ፕሮጀክቱ በ1989 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 172 የፕሮጀክት ጣቢያዎች አሉት። የደቡብ ክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ምትኩ ዳይማ እንደገለጹት የፕሮጀክት ጣቢያዎቹ ለስፖርቱ እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የለም። ፕሮጀክቶቹን አሉ ብሎ በቁጥር ለመጥቀስ ካልሆነ በቀር አመርቂ ስራም አልተሰራም። ታዳጊ ወጣቶች የሚመለመሉት የስፖርቱ ተግባራዊ እውቀት በሌላቸው ሰዎች መሆኑና የሚመለከተው አካል ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆን ፕሮጀክቶቹ ፍሬ አልባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የተመለመሉት ወጣቶች መረጃ አያያዝና አደረጃጃት ደካማ በመሆኑ የተስተካከለ ተክለ ሰውነት የመመልመል ክፍተትና የዕድሜ ማጭበርበር በስፋት እንደሚስተዋል አቶ ምትኩ ዘርዝረዋል። የአፋር ክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጋሻው ነጋ በበኩላቸው የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቱ ውጤታማ ያልሆነው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በስፖርቱ እምቅ አቅም ባላቸው ቦታዎች ላይ ባለማተኮሩ እንደሆነ ተናግረዋል። የደቡብና የጋምቤላ ክልሎችን አብነት በመጥቀስ በክልሎቹ ታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ተተኪ የቮሊቦል ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል በመጠቆም። በስልጠና ጣቢያዎች የትጥቅና የግብዓት ችግር መኖርና ሳይንሳዊ ስልጠና አለመስጠት በፕሮጀክቱ የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል። ስፖርቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆንና የተሰጠው ትኩረት ማነስ የታዳጊ ወጣቶች የቮሊቦል ፕሮጀክት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መልካም ጌታቸው ናቸው። በፕሮጀክቱ ላይ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል ሃላፊዋ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ የተነሱትን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ጥናት በዚህ ዓመት እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ከጥናቱ ባሻገር መልማዮች ስለ ስፖርቱ የሚያውቁ እንዲሆኑ ማድረግ፣ እምቅ አቅም ያላቸው አካባቢዎች ላይ መስራትና ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማሻሻል ትኩረት ይደረግባቸዋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የግብዓትና የትጥቅ ችግሩን እንዲሁም የፌዴሬሽኑን የበጀት እጥረት ለመፍታትም አማራጭ የገቢ ምንጮች ይፈለጋሉ ነው ያሉት። የፕሮጀክቱን ችግሮች ለማስወገድ ክልሎችና የሚመከታቸው አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። በሁለቱም ጾታዎች የቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ማቋቋም፣ የውድድር መድረኮችን ማስፋት፣ ስፖርቱን ከመንግስት የበጀት ድጎማ ማላቀቅ፣ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና የስፖርቱን ህዝባዊ መሰረት ማሳደግ የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የተለያዩ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች፣ ዳኞች፣ አሰልጣኞችና ባለድርሻ አካላት በጠቅላላ ጉባኤው ተሳትፈዋል። የቮሊቦል ስፖርት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር የውጭ አገራት መምህራን ስፖርቱን እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ፤ የስፖርቱ መዘውተርም በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል። ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየውን ቮሊቦል ለማነቃቃት በሁለቱም ጾታ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም