ቀጥታ፡

18 አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ የቮሊቦል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2011 የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ለ18 አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ የቮሊቦል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ሰጠ። አካዳሚው ከጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው ዓለም አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ የቮሊቦል አሰልጣኝነት ስልጠና ትናንት ተጠናቋል። በስልጠናው በሁለቱም ጾታ በድምሩ 18 የቮሊቦል የአንደኛ ደረጃ አሰልጣኞች የተሳተፉበት ሲሆን የዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን /ኤፍ.አይ.ቪ.ቢ/ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ስልጠናውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰልጣኞቹ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ወስደው የምስክር ወረቀቱን አግኝተዋል። ስልጠናው ከመጀመሩ በፊት 28 አሰልጣኞች ለአንድ ወር ከዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን ጋር በኢንተርኔት በመገናኘት የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ተሰጥቷቸው ፈተናም ተፈትነዋል። በንድፈ ሀሳብ ፈተና ከ80 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 18 አሰልጣኞች ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፍ ላለፉት አምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና ተከታትለዋል። እነዚህ አሰልጣኞች የተግባር ፈተና የወሰዱ ሲሆን በሁለቱም ዘርፍ ጥሩ ውጤት በማግኘታቸው ዓለም አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ የቮሊቦል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ማግኘት ችለዋል። በቮሊቦል ስፖርት ያለውን ተተኪዎችን የማፍራት ችግር መፍታት የአሰልጣኞቹ ቀጣይ ሃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል። ከፍተኛው የቮሊቦል አሰልጣኝነት ደረጃ ሶስተኛ ደረጃ መሆኑን ከዓለም አቀፉ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም