ቀጥታ፡

በቂ የህክምና ባለሙያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት የለም በሚል ምክንያት ላላስፈላጊ ወጪ ተዳርገናል-የካንሰር ህሙማን ታካሚዎች

ባህር ዳር ጥቅምት 10/2011 በቂ የህክምና ባለሙያና የመድኃኒት አቅርቦት የለም በሚል ምክንያት ላላስፈላጊ  ወጪ ተዳርገናል ሲሉ የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የካንሰር ህሙማን ታካሚዎች ገለጹ። የሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ማዕከል ሐኪሞች በባለሙያዎች እጥረት ምክንያት ለታካሚዎቹ ተገቢውን የህክምና አገልግሎትበመስጠት ላይ  አለመሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ታካሚዎቹ ለኢዜአ በቀጠሮ ብዛት ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ሦስት ሳምንታትን እንዳስቆጠሩ የሚናገሩት አቶ አባው እርስቱ  "እስካሁን ዛሬ፣ነገ በሚል ምላሽ ለህመሜ ፈውስ ካለማግኘቴም  በላይ  ላላስፈላጊ ወጪ እየተዳረግሁ ነው" ብለዋል፡፡ በየቀኑ ቀጠሮ የሚቀጥሩበት ምክንያት የሀኪም እጥረት ስላለ ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸውም  ገልጸዋል፡፡ ለህመማቸው ተገቢውን ህክምና ካለማግኘታቸውም በተጨማሪ በቀጠሮ ምክንያት የሚያወጡትን ወጪ መቋቋም አለመቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ጌታነው ሞገስ ናቸው። የባለሙያ እጥረትና መድኃኒት የለም የሚሉ  ምክንያቶች ከሀኪሞች እንደሚነገራቸው የገለጹት ታካሚው፣ በቀጠሮ ምክንያት ለማደሪያና ለምግብ ከፍተኛ ወጪ ስለሚያወጡ ለህክምና የያዙትን ገንዘብ እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡ ህሙማኑ የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል እንደሆነና በባለሙያ እጥረትና በቂ የመድኃኒት አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት የታካሚዎቹን ችግር ማቃለል እንዳልተቻ  ሀኪሞች ይናገራሉ። የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆሰፒታል ሀኪም የሆኑት ዶክተር ሰርካለም ዘውዴ እንደገለጹት በተለይ በካንሰር ህክምና ማዕከል ከፍተኛ የባለሙያዎችና የመድኃኒት እጥረት ይስተዋላል። እንደ ህሙማኑ የካንሰር ዓይነት መድኃኒቱ እስኪመጣ ድረስ ለህሙማኑ ቀጠሮ እንደሚሰጥ የተናገሩት ዶክተር ሰርካለም፤ከባለሙያዎችና ከመድኃኒት ጋር ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ ለሚመለከተው አካል በጽሁፍም ሆነ በቃል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም መፍትሄ ያለማግኘታቸውን አብራርተዋል። ዶክተር ሱፌ መሐመድ የተባሉት ሐኪም በበኩላቸው ማዕከሉ አንድ የካንሰር ህክምና ማዕከል ሊያሟላ የሚገባውን ግብዓት  ባለማሟላቱ  ህሙማኑ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ እንዲጉላሉና ህመማቸው እንዲባባስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ''ኃላፊነት እንደሚሰማው የጤና ባለሙያ ህሙማንን በምንችለው ልክ መርዳት አልቻልንም''ያሉት ዶክተር ሱፌ  "በመድኃኒት አቅርቦትና  በነርሶች እጥረት ምክንያት ህሙማኑ  ሲጉላሉና ለተጨማሪ ወጭ  ሲጋለጡ ስናይ ቅስማችን ይሰበራል” ብለዋል፡፡ የሆስፒታሉን  አመራሮች ችግሮችን እንዲፈቱና ተገቢው ህክምና እንዲሰጥ  በተደጋጋሚ ጥያቄ  ቢቀርብም፤ ከአንድ ዓመት በላይ ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጠ ገልጸዋል፡፡ በሆስፒታሉ የነርስ እጥረት እንዳለ ያረጋገጡት የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆሰፒታል  ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ ባዬ  ባለሙያዎችን  የሚቀጥረው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጠንም ይላሉ፡፡ ሐኪሞች የነርሶችን የማስታመም ሥራ ደርበው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣  በዚህም ምክንያት የታካሚወዎች መጉላላት መኖሩን አምነዋል፡፡ ችግሩ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ መሆኑንና ቢሮው የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ካልመደበ ችግሩ ሊባባስ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የመድኃኒት እጥረት የተከሰተው የካንሰር መድኃኒት ውድና በብዛት ስለማይገኙ መሆኑን አስረድተዋል። የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የሰው ሃብት ደጋፊ የሥራ ሂደት ተወካይ አቶ ሰለሞን አሰፋ ሆስፒታሎቹ  የሚጠየቁትን የሰው ኃይል ሙሉ በሙሉ ለማሟላት የባለሙያዎች እጥረትና የበጀትም ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የሆስፒታሉ  ህሙማንን  ቁጥር ከግምት ውስጥ  በማስገባት ከሌሎቹ ሆስፒታሎች በተለየ ሁኔታ በቂ ባለሙያዎች እንዲሟላለት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የተመደቡለትን ባለሙያዎች በአግባቡ ተቆጣጥሮ ማሰራት ከሆስፒታሉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ከጎንደር የካንሰር ማዕከል በመቀጠል  ሁለተኛው የካንሰር ማዕከል  የፈለገ-ህይወት የካንሰር ህክምና ማዕከል ከተቋቋመ 15 ወራትን አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም