ቀጥታ፡

በአዳማ በአንድ ቀበሌ የሰፈረው የዝንጀሮ መንጋ የማባረር ዘመቻ እየተካሔደ ነው

አዳማ ጥቅምት 10/2011 በአዳማ ከተማ በአንድ ቀበሌ የሰፈረው የዝንጀሮ መንጋ በጥይት ድምፅ አስደንብሮ የማባረር ዘመቻ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የከተማው ነዋሪዎች ግን እርምጃው መንጋውን በዘላቂነት ከአካባቢው የሚያባርር ስለመሆኑ እንጠራጠራለን ብለዋል ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የቀድሞው 09 የአሁኑ እሬቻ ቀበሌ ነዋሪዎችን በማነጋገር  ላለፉት 6 ዓመታት በዝንጀሮ መንጋው ቤታቸው ፈራርሷል ፣ የምግብ ፍጆታቸው በየጊዜው ተነጥቀዋል ፣ ቋሚ የፍራፍሬ ተክሎች ወድመዋል ፣ ነዋሪዎችም በስጋት ላይ ወድቀው ለመኖር ተገደዋል የሚል ዘገባ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አሰራጭቶ እንደነበር ይታወሳል። የአዳማ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የዝንጀሮ መንጋውን ለመቀነስ ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጎ እንዳልተሳካ ገልፆ አዲስ አማራጭ ለመተግበር መዘጋጀቱን በወቅቱ ገልፆ ነበር። በከተማው አስተዳደር የአካባቢ ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለማ አስፋው እንደገለፁት አዲሱ አማራጭ የዝንጀሮ መንጋውን በጥይት ድምፅ በመረበሽ ከአካባቢው ነቅሎ እንዲወጣ በማድረግ በህብረተሰብ አጀብ ወደ ቦኩ ጫካ ለማባረር የሚያስችልና ከ10 እስከ 15 ቀናት የሚዘልቅ ዘመቻ ተጀምሮ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። የከተማው አስተዳደር ሁኔታውን ለኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን በተደጋጋሚ በማሳወቅ በባህላዊ መንገድ መንጋውን ከከተማው ለማስወጣት የተደረገው ጥረት ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱን አቶ ለማ ይናገራሉ። ከፌዴራል የደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን አልሞ ተኳሾችን ሶስት ጊዜ በማስመጣት ዋና ዋና የመንጋው መሪዎች በመግደል ለመቀነስ የተደረገው ጥረትም ከጊዜአዊ መፍትሄነት የዘለለ ባለመሆኑ አዲስ አማራጭ መተግበር ማስፈለጉን ነው የተናገሩት። የዝንጀሮ መንጋው አደንዝዞ ወደ እንስሳት መኖሪያ ፓርክ ለማጓጓዝ ቴክኖሎጂው በአገሪቱ አለመኖሩ ችግሩ ውስብስብ እንዳደረገው የገለፁት አቶ ለማ ''ምናልባትም አዲሱ አማራጭ መፍትሔ ሊሆን ይችላል'' ብለዋል። የችግሩ ሰለባ ሆነናል የሚሉት የከተማው ነዋሪዎች ግን አፋጣኝ መፍትሄ ባለመወሰዱ የዝንጀሮ መንጋው ቁጥሩ ጨምሮ ፣ የሚያደርሰው ጥፋት ተባብሶ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ። በቀበሌው የህብረተሰቡ ተወካይ አቶ ጉታ ጎንፋ እንደሚሉት በዝንጀሮ መንጋው ለጉዳት የተዳረጉት አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪዎች በጡረታ ክፍያ የሚተዳደሩና አቅመ ደካሞች ናቸው። በዝንጀሮ መንጋው የቤታቸው ጣራና ቆርቆሮ እየተነቃቀለ ፣ የእለት ጉርሳቸው ሳይቀር እየተነጠቁና የሰሩትን ቤት ለመሸጥ እንኳን በችግሩ ሰበብ ገዥ መጥፋቱን ፣ ተከራይ ማግኘት ደግሞ የማይታሰብ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል። ዝንጀሮውን ለማባረር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በመንጋው የፈራረሱት ቤቶቻችን ለመጠገን እንዲያግዘን የቆርቆር እርዳታ እንዲደረግልን ሲሉም  አቶ ጉታ ጠይቀዋል። ''አሁን ዝንጀሮዎችን ለማስደንገጥ እየተተኮሰ ያለው መሳሪያ ድምፁ አነስተኛና ጧትና ማታ ብቻ ለውስን ሰዓታት የሚካሄድ ስራ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ስለማምጣቱ እጠራጠራለሁ'' ብለዋል። ስራው ቀኑን ሙሉ ቢከናወንና የተሻለ መሳሪያ ጥቅም ላይ ቢውል ግን ምናልባትም መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል ። በአካባቢው ለ22 ዓመታት መኖራቸውን የገለፁት አቶ ፋሲል አዌቱ በበኩላቸው ላለፉት ስድስት ዓመታት የዝንጀሮ መንጋውን የሚያስከትለው ጉዳት እንዲቀረፍላቸው አቤት ያላሉትና ያልሄዱበት መስሪያ ቤት አለመኖሩን ይናገራሉ። ለህዝቡ አቤቱታ ተገቢው መፍትሔ ባለመሰጠቱ ምክንያት የመንጋው ቁጥር እየጨመረ የሚያደርሰው ጉዳት ደግሞ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል። አሁን መንጋውን ለማባረር የተጀመረው ዘመቻ የሰው ሃይልና መሳሪያ በመጨመር ተከታታይነት ባለው መልኩ ቀኑን ሙሉ ቢካሄድ መፍትሄ ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። አቶ ሃይሉ ማሞ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለፁት የመንጋው ቁጥር ከአንድ ሺህ ይበልጣል። መንግስት የተቀናጀና የተደራጀ እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር በአሁኑ አካሄድ መንጋው ማባረር ይቻላል የሚል እምነት የለኝም ብለዋል። ነዋሪዎቹ የተሻለ አማራጭ አድርገው የሚወስዱት መንጋው አደንዝዞ ወደ እንሰሳት መኖሪያ ፓርክ ቢወሰድላቸው ነው ። የከተማው አስተዳደር ደግሞ የማደንዘዣውም ሆነ የማጓጓዣው ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ የለም  የሚል ምላሽ ሰጥቷል። የተጀመረው ዘመቻ በጥናት ላይ ተመስርቶና የመንጋውን ማዳሪያ ተለይቶ እየተካሄደ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ይሳካል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ለማ አስፋው ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም