ህገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል ፖሊስ እና ደንብ ማስከበር በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 በአዲስ አበባ እየተስተዋለ ያለውን ህገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽንና ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ። የተቋማቱ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ ባወጡት እቅድ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። የተካሄደውን ውይይት በተመለከተ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ጨምሮ ሌሎችም ህገ-ወጥ ተግባራት እየተበራከቱ መጥተዋል። በዚህም ለወንጀል መስፋፋት መንስኤ በሆኑ ጫት ማስቃም፣ ሺሻ ማስጨስ እና ቁማር ማጫወት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተገልጿል። በተለይ ደግሞ የተደራጁ ወንጀለኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አስረድቷል። የኮንትሮባንድ፣ ህገ-ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ እና የመሬት ወረራን በመከላከል የህግ የበላይነትን ለማስፈን ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ስራዎችን ሊያሰራ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባት ወሳኝ መሆኑንም ኮሚሽኑ ጠቁሟል። የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት በበኩሉ ደንብን የማስከበር ስራ ለተቋማቱ ብቻ የሚተው እንዳልሆነ አመልክቷል። በዚህም ህግን ለማስፈንና ህገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ትብብራቸውን አጠናክረው አንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም