የዲላ ከተማ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ያሳየውን ጽናት እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዲላ ከተማ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ያሳየውን ጽናት እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ዲላ ጥቅምት ጥቅምት 9/2011 የዲላ ከተማ ፖሊስ በ2010 ዓ.ም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ያሳየውን ጽናት በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል የከተማው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ የከተማዋ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በ2010 የነበረውን አፈጻጸም ከነዋሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡ በመድረኩ ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተሾመ ጂግሶ እንዳሉት በ2009 በዲላና ሌሎች የጌዴኦ ዞንኖች፣ ከተማና ወረዳዎች ላይ ተከስቶ ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ በተወሰኑ የፖሊስ አባላት ላይ የወታደራዊ ሥነ-ምግባር ጥሰቶች ታይተው ነበር። በእዚህም ምክንያት ፖሊስ በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ተአማኒነት ተሸርሽሮ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ከክስተቱ በኋላ የከተማዋ ፖሊስ መዋቅር ራሱን ገምግሞ ወደለውጥ በመግባቱ መሻሻሎች መምጣታቸውን አቶ ተሾመ ተናግረዋል ፡፡ በከተማዋ ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ የነበረውን የቡድን ፀብ ፖሊስ ከማብረድ ጀምሮ በአጎራባች ዞኖች የተከሰተው የፀጥታ ችግር ወደ ዲላ ከተማዋ እንዳይዛመት ያከናወናቸው ተግባራትን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የከተማው ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ባከናወናቸው ሥራዎች በ2009 የነበረውን ሥም ከመቀየር ባለፈ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ያጠናከረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የከተማዋ ፖሊስ በ2010 ያሳየውን ጽናት አጠናክሮ መቀጠል አለበት" ያሉት አቶ ተሾመ በተለይ በአሁኑ ወቅት በከተማው እየታየ ያለውን የተደራጀ የስርቆት ተግባር ለመከላከል ጠንክሮ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡ ወጣት ኤፍሬም ግርማ በበኩሉ ባለፈው ዓመት በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖችና በጌዴኦ ዞን አጎራባች አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መፈናቀላቸውን አስታውሷል፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ቀስቃሽ አጀንዳዎችን በማራመድ የከተማዋን ህዝብ ለመከፋፈልና በ2009 የነበረውን መጥፎ ታሪክ ለመድገም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተናግሯል ፡፡ ወጣት ኤፍሬም አንዳለው ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ ሌት ተቀን በመስራቱ የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ ተጠብቆ ሊቆይ ችሏል ፡፡ ፖሊስ በሠላም ጉዳይ ላይ ያሳየውን ትጋት በሌሎች ተግባራት ላይም ሊደግም እንደሚገባ የጠየቀው ወጣት ኤፍሬም በተለይ ሺሻና ጫት ቤቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክቷል ፡፡ የዲላ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ መሀመድኑር አብራር በበኩላቸው " ፖሊስ በሰላም ጉዳይ ላይ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የፈጠረው ቁርኝት ውጤት እያመጣ በመሆኑ ሊቀጥልበት ይገባል" ብለዋል። ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት ቅድመ መከላከል ላይ በስፋት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡ በ2010 ፖሊስ በሰላም ላይ ላመጣው ውጤት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም የደምብ አስከባሪዎችና የከተማው ህዝብ አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ሳጅን ጴጥሮስ ዘለቀ ናቸው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በመድረኩ የተሰጡትን ጠቃሚ ግብአቶች በመውሰድ ቀጣይ ስራዎችን በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት አዛዡ በተለይ ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት ቀድሞ ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን ለማጠናከር እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ እንደ ምክትል ሳጅን ጴጥሮስ ገለጻ በከተማዋ የሚታየውን የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የተደራጀ ሌብነትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል በ2011 በትኩረት የሚሰራ ሲሆን ለዚህም የፖሊስ ኃይሉን ለማጠናከር ዕቅድ መያዙን ተናግሯል ፡፡ በከተማው በሺሻ ቤቶች ላይ ፖሊስ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን የተናገሩት ምክትል ሳጅን፣ በቀጣይ ለዘላቂ መፍትሄ ከዲላ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ጥናትን መሰረት ያደረገ ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አብራርተዋል ፡፡ መድረኩ ላይ የተገኙት የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ "የከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ፖሊስ የሚኖረው ድርሻ የላቀ ነው" ብለዋል፡፡ ፀጥታን ከማስከበር ባለፈ በከተማዋ ህጋዊ የንግድ ሥርአትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፖሊስ ጋር የበለጠ ግንኙነት ፈጥረው እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡ በመድረኩ ከ20 ዓመታት በላይ በፖሊስነት ላገለገሉ ዘጠኝ የከተማው ፖሊስ አባላት የአገልግሎት ዘመን የወርቅ ሪቫን ሽልማት ተበርክቷል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው ፡፡