ቀጥታ፡

አትሌት ብርቱካን አደባና አትሌት እዮብ ዓለሙ ለአራት ዓመታት ከስፖርታዊ ውድድሮች ታገዱ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 አትሌት ብርቱካን አደባ እና አትሌት እዮብ ዓለሙ አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው በመገኘታቸው ለአራት ዓመታት በየትኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ ቅጣት ተላለፈባቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አትሌት ብርቱካን አደባ ህዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም በቻይና የሻንጋይ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር በአበረታች ቅመሞች ምርመራ የተከለከለ መድሃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት መጸፈሟ ተረጋግጧል። በተደረገው የምርመራ ውጤትም አትሌቷ "ኤክሶጄነስ ስቴሮይድ" የተባለ የተከለከለ መድሃኒት ተጠቅማ የተገኘች መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በተመሳሳይ አትሌት እዮብ ዓለሙ ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም በቻይና ሎንግኩ ዓለም አቀፍ ማራቶን የተከለከለ መድሃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት መፈጸሙን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በአትሌቱ ላይ የተደረገው የምርመራ ውጤት "ኢሪትሮፖይቲን" የተሰኘ የተከለከለ መድሃኒት ተጠቅሞ እንደተገኘ ታውቋል። በመሆኑም የጽህፈት ቤት የዳኝነት አካል አትሌቶቹ ለአራት ዓመታት በማንኛውም አገራዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና በየትኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ ቅጣት አስተላልፎባቸዋል። በቀጣይም አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ-አብረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የፀረ-አብረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ ላይ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊው አትሌት ሐይሌ ቶሎሳ በ2008 ዓ.ም ፔሩ ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር እንዲሁም አትሌት አሊ አብዶሽ በ2009 ዓ.ም በቻይና ጉዋንዡ በተካሄደው የማራቶን ውድድር አበረታች መድሐኒት በመጠቀማቸው የአራት ዓመት ቅጣት እንደተላለፈባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም