የተሻለ የእንቁላል ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎች ለአርቢዎች ሊሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሻለ የእንቁላል ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎች ለአርቢዎች ሊሰራጩ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 በኢትዮጵያ በምርምር የተገኙና የተሻለ የእንቁላል ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎች በቅርቡ ለአርቢዎች እንደሚሰራጩ የግብርና ሚንስቴር ገለፀ፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ የዶሮ ዝርያዎች መካከል በዓመት እስከ ሁለት መቶ እንቁላል ምርት የሚሰጡ ይገኙበታል። በኢትዮጵያ ያሉት የዶሮ ዝርያዎች ግን ዓመታዊ የእንቁላል ምርት ከሰባ አይበልጥም። ለዚህም የሚጠቀሱት ዋናዎቹ ፈተናዎች ምርታማ የሆኑ ዝርያዎች አጥረት፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት አለመኖርና ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ እጦት ናቸው ሲል የግብርና ሚንስቴር አስታውቋል። ይህንን ችግር በመቅረፍ የዶሮ ልማትን ለማጠናከር የተለያየ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ያመለከተው ሚኒስቴሩ በእስካሁኑ ትግበራም ውጤት እየታየ ነው ብሏል። በዚህም መሰረት በደብረዘይት የምርምር ማዕከል በዓመት እስከ 180 እንቁላል ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎች በምርምር መገኘታቸውን በሚንስቴሩ የዶሮ ኃብት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽጌረዳ ፍቃዱ ለኢዜአ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅትም በምርምር የተገኙት የዶሮ ዝርያዎች የውጪውን አየር መቋቋም መቻላቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርምር እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሯ ነግረውናል፡፡ ምርምሩ በመጠናቀቅ ሂደት ላይ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የሚቀረው ተግባር ዝርያዎቹን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዶሮ ኃበት ልማትን በማስፋፋት ተዋፅኦውን ማጎልበት እንዲቻል በሥጋም ሆነ በእንቁላል ምርታማነታቸው ጥምር ጠቀሜታ ያላቸውን የዶሮ ዝርያዎች ከውጭ ሀገራት በማስገባት ምርምር ሲደረግ መቆየቱንም ወይዘሮ ጽጌረዳ ተናግረዋል፡፡ ምርምር ከተደረገባቸው አምስት የዶሮ ዝርያዎች ውስጥ ሶስቱ የተሻለ ውጤት በማምጣታቸው ተለይተዋል ብለዋል፡፡ የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ የተለዩት እነዚህ ሶስት የዶሮ ዝርያዎችን በሀገር ደረጃ ለማሰራጨት ዝግጅቱ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። ፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶሮዎች እንዳሉ ሲነገር በኢትዮጵያ ያለው የዶሮ ኃብት ግን ከ60 ሚሊዮን አይበልጥም። የዶሮ ምርት ተዋፅኦዎችን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት የሰጠ ሲሆን ዘርፉ በፍኖተ ካርታ ውስጥ የተካተተ መሆኑም ተመልክቷል። በቀጣይም በዘርፉ የባለኃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሚንስቴሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ ወይዘሮ ጽጌረዳ ተናግረዋል፡፡