የኢትዮ-ካናዳ የሁለትዮሽ ምክክር በኦታዋ ተጀመረ

63
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 7ኛው የኢትዮ-ካናዳ የሁለትዮሽ ምክክር ትናንት በካናዳ ኦታዋ ከተማ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከተ። በሚኒስቴሩ የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል በአቶ ነቢያት ጌታቸው የሚመራ ልዑክ ከካናዳ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢያን ሹጋርት ጋር ተወያይቷል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ መልካም ግንኙነት በማንሳት የጋራ ጉዳዮች በሆኑ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። የልዑካን ቡድኑ ቆይታ በሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትብብር ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሁለትዮሽ ምክክር ውይይቱ በዛሬው ዕለትም ይካሄዳል። ኢትዮጵያ እና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም እንደሆነ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሁለቱ አገሮች በፖለቲካና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሲሆን ካናዳ ድህነትን በመዋጋት፣ በምግብ ዋስትናና ግብርና ልማት ለኢትዮጵያ ልማት ድጋፍ ታደርጋለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም