ቀጥታ፡

የህግ ጥሰት ለሚፈፀምባቸው ሴቶችና ህጻናት ነጻ የህግ አገልግሎት ለመሰጠት ፍላጎት እንዳላቸው የህግ ባለሙያዎች ገለፁ

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 በአዲስ አበባ ህግ ጥሰት ለሚፈፀምባቸው ሴቶችና ህጻናት በበጎ ፍቃድ ነጻ የህግ አገልግሎት ለመሰጠት ፍላጎት እንዳላቸው የህግ ባለሙያዎች ገለፁ። በከተማው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ  ሥር ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮች የሚገኙት የህግ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ቀልጣፋና ጥራት ያለው ነጻ የህግ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ቢሮው አስታውቋል። ቢሮው የሚሰጠውን ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ለማጠናከር ከበጎ ፍቃደኛ የህግ ባለሙያዎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የህግ ባለሙያዎች እንደገለጹት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት በበጎ ፍቃድ ሙያዊ ድጋፍ፣ የማማከር፣ ጥብቅና መቆምና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው። ከዚህም ሌላ በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሥር ላሉ የህግ አገልግሎት አካላት የስራ ልምዳቸውን ለማካፈልና አስፈላጊውን የሙያ ስልጠና ለመስጠትም ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ቢሮው ተደራራቢ ኃላፊነት የሌለባቸውን አዳዲስ ባለሙያዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ  በማዕከል፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚገኙ የህግ ባለሙያዎችን ውጤታማነት ለማጎልበት ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስራ ማካሄድ እንዳለበትም አሳስበዋል። ከዚህም ሌላ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻልና የህግ ክፍሎቹን ግብት የማሟላት ተግባርም ከቢሮው የሚጠበቁ መሆናቸውን አንስተዋል። በተለያዩ የፍትህ ተቋማትን ጨምሮ በግል የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎችም የተወሰነ ጊዜያቸውን ለነፃ የህግ አገልግሎት የበጎ ተግባር እንዲያውሉ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሪት ሜሮን አራጋው ቢሮው ለሴቶችና ህጻናት የሚሰጠውን ነጻ የህግ አገልግሎት ለማሻሻል የባለሙያዎችን አቅም የመገንባትና ግብዓቶችን ለማሟላት የተጀመሩ ስራዎች አሉ ብለዋል። በማዕከል፣ በክፍለ ከተማና በወረዳዎች የሚገኙ የህግ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ቀልጣፋና ጥራት ያለው ነጻ የህግ አገልግሎት መሰጠት አለመቻሉን ነው የገለጹት። በመሆኑም በበጎ ፍቃድ የሚሳተፉ የህግ ባለሙያዎች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የብዙ ዓመታት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ድጋፍ ማነስ፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ለሴቶችና ህጻናት ጥቃት ተቋርቋሪ ያለመሆን ፣ የበጀት ማነስና ሌሎች ከነጻ የህግ አገልግሎት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውንም አንስተዋል። ቢሮው ነጻ የህግ አገልግሎት ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከልም የሴትና የወንዶች ህጻናት አስገደዶ መደፈር ፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ፣ የአባቶች ልጅን መካድና የልጅ ቀለብና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ አንደሚገኙባቸው ገልፀዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ቢሮው ለ13 ሺህ 500 ሴቶችና ህጻናት ነጻ የህግ አገልግሎት ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም