የእንስሳት ኃብት ተዋጽኦና የዶሮ አውደ ርዕዩ የገበያ ትስስርና የቴክሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ያግዛል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ኃብት ተዋጽኦና የዶሮ አውደ ርዕዩ የገበያ ትስስርና የቴክሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ያግዛል ተባለ
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 አራተኛው የአፍሪካ የእንስሳት ኃብት ተዋጽኦና የዶሮ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ መካሄድ በአገሪቱ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ ጠንካራ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የቴክሎጂ ሽግግር ለማድረግ ያገዛል ተባለ። ለመጪዎቹ ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው አውደ ርዕይ ላይ የአሜሪካ፣ ቤልጄም፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ሃንጋሪ፣ ህንድ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድ፣ ፓኪስታንና ሱዳንን ጨምሮ ከ13 አገራት የተወከሉ 60 ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ ወረስ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት የአውደ ርእዩ መዘጋጀት በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍና ዘርፉነ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተመክሮዎችን ለመቅሰም ያግዛል። በአውደ ርእዩ ከዘረፉ እድገትና ልማት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አገራት ቴክኖሎጂዎች፣ የግብይት ስርዓትንና እውቀት የሚቀርብበት በመሆኑ ልምድ ይወሰድበታል ብለዋል። የውጭ አገራት ኩባንያዎ ለአውደ ርእዩ ወደኢትዮጵያ መምጣታቸው በእንስሳት ኃብት ተዋጽኦ እና በዶሮ ርቢ ዘርፍ በአገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል ለማስተዋወቅም ያስችላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። በአገሪቱ ያለውን ሰፊ የገበያ ፍላጎት ለመሸፈንና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን የገበያ መዳረሻ ለማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል። የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎችም ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ሁነቱ እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ በዘርፉ ልማት የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም በተለይ ከስፔኑ ሊፕቶዛ ኩባንያ የመጡ ተሳታፊ ገልፀዋል። አቶ ዳኒኤል ከአልማ ፋርምስ እንገጹት "ነባር እና አዳዲስ ምርቶቻችን ለማስተዋወቅ፣ አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት፤ ሌሎች ምርቶችን ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር ለመገናኘት ይረዳናልእንዲሁም የተለያዩ ምረቶች ፤ ያለቀላቸው የእንስሳት መኖዎች፤ ዶሮ ፤ እንቁላል፤ የጫጩቶች፤ የስጋና ሌሎች ምርቶች አሉን"ብለዋል፡፡ ድርጅታቸውን የሚያመርተውን ምርቶች ለማስተዋወቅ፤ መግዛት ለሚፈልጉም እንዲገዙና በተጨማሪም የድርጅቱን ገጽታ ለማስተዋወቅ ያግዘናል" ያሉት ደግሞ አቶ ብሩክ የማነህ ከኢትዮ ፊድ ናቸው ። አውደ ርእዩን 5 ሺህ ጎብኝዎች ይጎበኙታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግርን መሰረት ያደረገ የንግድ ልውውጥና የአገር ውስጥ የገበያ ትስስር መድረኮች ይኖሩታል። የንግድ ትርኢቱን ፕራና ኤቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ያደረገው ኤክስፖ ቲም፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት በትብብር አዘጋጅተውታል።