ቀጥታ፡

የሆንግ ኮንግ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት አላቸው

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 የሆንግ ኮንግ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገለፁ። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሆንግ ኮንግ ቢዝነስ ልማት ምክር ቤት ጋር ያዘጋጀው የሆንግ ኮንግ የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ትስስር ፎረም ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። በዚሁ ወቅትም በኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አማካኝነት በሀገሪቱ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ከሆንግ ኮንግ ለመጣው ልዑካን ገለፃ ተደርጓል። ፋርማሲ፣ የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ማምረት እንዲሁም ጨርቃጨርቅና አልባሳት በመድረኩ ላይ ከቀረቡት የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከል ናቸው። ሆንግ ኮንግ ቢዝነስ ልማት ምክር ቤት ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ራይመንድ ይፕ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቢዝነስ ልዑኩ የመጣው በኢትዮጵያ ያሉትን የቢዝነስ አማራጮች ለማጥናት ነው። ጥቂት የሆንግ ኮንግ ባለሃብቶች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል። ወደፊትም እነዚህን ጨምሮ በግብርና ኢንደስትሪ ማቀነባበሪያ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ እና በሌሎች ምቹ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት መድረኩ ልዑካኑ ሊሰማሩባቸው የሚሉባቸውን ዘርፎች ለመምረጥ እድል የሚፈጥር ነው። ኮሚሽኑ ለቢዝነስ ልዑካኑ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማሳየት በተጨማሪ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የቢዝነስ ልዑካኑ በሶስት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታው የኢንደስትሪ ፓርኮችንና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እንደሚጎበኝ ይጠበቃል። የሆንግ ኮንግ ባለሃብቶች በሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ከተሰማሩት የተለያዩ አገራት የውጭ ባለኃብቶች መካከል ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም