ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ላይ የሚታዩትን የጥራት ችግሮች ለመቅረፍ ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአገሪቷን የጥራት መሰረተ ልማት በማሻሻል በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ላይ የሚታዩትን የጥራት ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገለጸ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ 'የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በማዋሃድ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር' መወሰኑ ይታወሳል። ሚኒስቴሩ "በቆዳና በቆዳ ውጤቶችን ጥራት ለማስጠበቅ እየሰራ ባለው "የጥራት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት" ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍስሃ እንደገለጹት፤ መንግስት የቆዳና የቆዳ ውጤቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ተቋማትን አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። ''ተቋማቱ ባላቸው የአቅምና ተቋማዊ ውስንነት የሚሰጧቸው አገልግሎቶች በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ጥራታቸውን የጠበቁ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርትና አገልግሎትን ማቅረብ ላይ ተፅህኖ እያሳደረ ስለሆነ ፕሮጀክቱን ቀርፆ መንቀሳቀስ ተገቢ ሆኗል'' ብለዋል። ስለሆነም ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባ የስራ ደህንነትን የማረጋገጥ፣ የጥራት ባህልን የማዳበርና የውጭ ምርትን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ በሱፍቃድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በቆዳ ወጪ ንግድ የዓለም የንግድ ሰንሰለት ውስጥ በስፋትና በጥራት ተጠቃሚ እንድትሆን የጥራት ማሻሻያ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል። የግል የጥራት ኩባንያዎች እንዲስፋፉ ማገዝ፣ አምራቾች በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ያለውን አስገዳጅና ተፈላጊ የጥራት ደረጃዎን እንዲያውቁና እንዲተገብሩ ማስቻል በጥራት ማሻሻያ ስራው እንዲካቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎቶችን በስፋት ተግባር ላይ ማዋልና አምራቾች ስለጥራት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ሌላው በማሻሻያ ስራው መካተት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ አብዛኛው የጥሬ ቆዳ ህብረተሰቡ በሚያደርጋቸው የእርድ ወቅት የሚገኙ በመሆናቸው ህዝቡ ለቆዳ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከጥሬ ቆዳ የሚጣል ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ የቆዳውን ጥራት በመጠበቅ ዋጋው ከፍ እንዲል በእንስሳት እርባታ ወቅት፣ በእርድና ለገበያ ሲቀርብ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ይህም ከውጭ የሚገባውን ቆዳ በማስቀረት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ የአገሪቷን የቆዳ የወጪ ምርት በ33 በመቶ ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም በአውሮፓና በአሜሪካ የኢትዮጵያ የወጪ ምርት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ጨርቃ ጨርቅና የአግሮ ፕሮሰሲንግን ጨምሮ በ20 በመቶ እንዲያድግ ያስችላል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትና የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽህፈት ቤት ተግባራዊ ይደረጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም