የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት የልምድና የዕውቀት ልውውጥ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዘናል- የመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች፡፡ - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት የልምድና የዕውቀት ልውውጥ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዘናል- የመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች፡፡
ሃዋሳ ጥቅምት 8/2011 የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት የልምድ ልውውጥ በማድረግ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው የመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የሀዋሳ በቆሎ ምርምር መለስተኛ ማዕከል ያዘጋጀው የመስክ ቀን በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ተከብሯል፡፡ የወረዳው አርሶ አደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የመስክ ጉብኝቱ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተሻለ ዝርያ ከመምረጥ አኳያ ልምድ ያገኙበት ነው፡፡ በመስቃን ወረዳ ሸርሸራ መች መና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዬ ላላ በጉብኝቱ አራት የበቆሎ ዝርያዎችን ማየት መቻላቸውን ገልጸው ከእነዚህ ዝርያዎች የፕሮቲን ይዘት ያለውንና የተሻለ ምርት የሚሰጠውን ቢኤች ኪው ፒዋይ 545 የተሰኘውን የበቆሎ ዝርያ በቀጣይ ለመጠቀም መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በአርሶ አደር ማሳ ላይ እየተሞከሩ ካሉ ዝርያዎች ውስጥ 'ኤም ኤች 138 ኪው' የተሰኘው የበቆሎ ዝርያ ችግር እንዳለበት የገለጹት አርሶ አደሩ የምርምር ማዕከሉ በቀጣይ በዝርያው ላይ ተጨማሪ ምርምር እንዲያደርግበት ጠይቀዋል፡፡ የጉብኝቱ ተሳታፊ ሴት አርሶ አደር አረጋሽ ጥላሁን በበኩላቸው የመስክ ጉብኝቱ መደረጉ ተጨማሪ እውቀትና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ቢኤች ኪው ፒዋይ 545 የተሰኘውን የበቆሎ ዝርያ ቀደም ሲል ተካሂዶ በነበረ የመስክ ጉብኝት በዓል ላይ መርጠውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የመስቃን ወረዳ አርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል አወል እንዳሉት በወረዳው ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በበቆሎ እንደሚለማ ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ፈጥነው የሚደርሱ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን የማላመድ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይ ከሀዋሳ በቆሎ ምርምር መለስተኛ ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር ከስድስት በላይ ምርታማ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚለሙ የፕሮቲን በቆሎ ዝርያዎች ላይ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ቢ ኤች 545፣ 546ና 547 በወረዳው የተለያየ አየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች ተሞክሮ የተሻለ ምርታማ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የሀዋሳ በቆሎ ምርምር መለስተኛ ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ መሰለ ኃይሌ እንዳሉት የመስክ ቀኑ አርሶ አደሩ የሚሆነውን ዝርያ እንዲመርጥና ልምድ እንዲለዋወጥ ያግዛል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተገኙ አርሶ አደሮች የተሻሻለውን ዝርያ ከመምረጥ ባለፈ ዝርያዎቹ ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ለምርምር የሚያግዝ ጥቆማ እንደተገኘበት ገልጸዋል፡፡ የጉብኝቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች የፕሮቲን ይዘት ያለውን የቆሎ ዝርያ እንደመረጡ የገለጹት ተመራማሪው የምርምር ማዕከሉ ተግባር ዝርያን ማሻሻልና ማውጣት ላይ በመሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የመስከ በዓሉ ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን ከመስቃን ወረዳ የተውጣጡ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡