ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃታል ተባለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለፈው ሳምንት አስታውቋል። መንግስት ይህን ያስታወቀው የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ በሚያመላክተው የፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ንግግር ነው። በተወሰኑ የዓለም አገራት አማካኝነት የተጠነሰሰው የንግድ ድርጅት በመላው ዓለም የሚካሄዱ የንግድ መስተጋብሮችን የሚመራ ዓለም አቀፍ ህግን መተግበር አንዱ ዓላማው ነው። በዓለም አገራት መካከል ነፃ የንግድ ግንኙነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ድርድሮች የሚካሄዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲሁም በንግድ መስተጋብሮች ሂደት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታትም የድርጅቱ ዓላማዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የዚህ ድርጅት አባል መሆን በምትችልበት መንገድ ላይ መደራደር ከጀመረች 15 ዓመታት ተቆጠረዋል። ከዚህ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሁለት ምሁራን የድርጅቱ አባል መሆን አገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጋት መሆኑን ይስማማሉ። የገበያ ጥናት ምሁሩ ዶክተር ጌቴ አንዱአለምና የምጣኔ ኃብት ምሁሩ ዶክተር ካሳ ተሻገር  እንደሚሉት አገሪቱ የደርጅቱ አባል ብትሆን የምታገኛቸው አያሌ ትሩፋቶች እንዳሉ ሁሉ ከባድ ፈተናዎችም የሚያጋጥሟት በመሆኑ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት ይጠይቃታል። ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ እንቀስቃሴ ውስጥ የሚገባትን ጥቅም ታገኝ ዘንድ መንግስት ትልቅ የቤት ስራ ከፊቱ እንዳለበትም ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን አገሪቱ አባል በመሆኗ የተለያዩ እድሎች ያሏት ቢሆንም በጊዜው ላይ ምሁራኑ የተለያዩ አመለካከት አላቸው። ዶክተር ጌቴ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ውስጥ የሚታዩትን ምስቅልቅሎች ለማስተካከል የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የሚጠቅም በመሆኑ በተቻለ ፍጥነት ድርጅቱን መቀላቀል ይገባል ሲሉ ዶክተር ካሳ በበኩላቸው ሌሎች በርካታ ቀደም ብሎ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ያሉ በመሆኑ አባል ለመሆን መቸኮል አይገባም ባይ ናቸው። ዶክተር ጌቴ እንደሚሉት በአገሪቱ እየተገነባ ያለው ፖለቲካና በፋይናንሰ ተቋማት ላይ የተወሰደው የፖሊሲ እርምጃ በማጠናከር  ወደ አባልነቱ የሚደረገውን ጉዞና አሁን እየታየ ያለውን እድል መጠቀም ይገባል፡፡ ይህንን እድል ለመጠቀም የግሉና የመንግስት ተቋማት በዓለማቀፉ የንግድ አሰራር እንዲቃኙ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል። በአገሪቱ ቀጣይነት ያለው የተረጋጋ ፖለቲካ ማስፈን፣ የመንግስትና የግል ተቋማት ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት አቅም ለማጠናከር ሰፊ ስራ መስራት አለበትም በማለት ገልፀዋል። አገሪቱ በቅርቡ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ዶክተር ጌቴ ይደግፋሉ። ዶክተር ጌቴ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ቢያገኝ  በአገሪቱ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚታየው ውስብስበ ችግርን ለመፍታት የሚያስችል መልካም ሁኔታ ይፈጠራል። በተለይም በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለው የዋጋ መዋዥቅ፣ ህገ-ወጥ የንግድ አሰራር፣ በአጠቃላይ ውጤታማና ተወዳዳሪ  ድርጅቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትና አገሪቱ ከዘመናዊና ከአለም የንግድ አሰራር ስርዓት ጋር በቅርበት የምትሰራበት እድል ይኖራል ይላሉ ዶክተር ጌቴ። ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን መቸኮል የለባትም፤ በርካታ በአገር ውስጥ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት አሉ ባይ ናቸው። "አሁን ባለን አቋም ወደ አባልነቱ ባንቀላቀል ይመረጣል" የሚሉት ዶክተር ካሳ በአገሪቱ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በምርቶችና  በአገልግሎቶች ላይ የሌሎች አገራት የበላይነት ይሰፍናል፣ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም ጥቅም ይቀንሳል ይላሉ። ስለዚህም መንግስት በነጻ ገበያውና ወቅቱ በሚጠይቀው ዓለማቀፍ ህግ ተቋማትንና ፖሊሲዎቹን ቢዳሰስ መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ። የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በተለያዩ አገራት የሚካሄዱ ድርድሮች ከ10-25 አመታት እንደሚወስድ መረጃዎች ያሳያሉ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ሳምንት ለህዝብና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ሲከፈት እንዳሉት መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ዕቅድ እውን ለማድረግ እየተሰራ ያለውን የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባልነት አጠናክሮ ይቀጥላል። ተገቢውን ድርድር ለማከናወንም በፖለቲካ አመራሩ የቅርብ ድጋፍ የአገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ ሁኔታና በተቀናጀ አሰራር ሂደቱን ከግብ ለማድረስ ይሰራልም ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም