ሴቶች ብልሃትና ጥበብ በተሞላበት መንገድ የመምራት አቅም አላቸው - የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች ብልሃትና ጥበብ በተሞላበት መንገድ የመምራት አቅም አላቸው - የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ባህር ዳር ጥቅምት 8/2011 በሃገሪቱ በከፍተኛው የስልጣን ደረጃ የተቀመጡት ሴት አመራሮች ብልሃትና ጥበብ በተሞላበት መንገድ በመምራት ''ሴቶች አይችሉም'' የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ይሰብራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሁለት ሴት ምሁራን ገለፁ። በዩኒቨርሲቲው የጎልማሶችና ማህበረሰብ ልማት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ጥሩወርቅ ዘላለም ለኢዜአ እንደገለጹት ሴቶች አቅም ቢኖራቸውም እምነት ተጥሎባቸው ወደ ከፍተኛ አመራርነት በማምጣት በኩል ውስንነት ነበር፡፡ በከፍተኛ አመራርነት የተመደቡ ጥቂት አመራሮች ግን ጠንካራና ውጤታማ ስራ ሲሰሩ እንደሚመለከቱ ተናግረዋል፡፡ አመራርነት ፆታን ሳይሆን ብቃትና ችሎታን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ረዳት ኘሮፌሰሯ አሁን ወደስልጣን የመጡ ሴት አመራሮችን በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በማጠናከር በኩል የተሻለ ስራ ይሰራሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ ''ከሴት አመራሮች የምንጠብቀው እስካሁን የተነፈግነውን ዕድል ስናገኝ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉና ተፈጥሮ የለገሰችንን የሴትነት ብልሃት፣ አስተዋይነትንና የእናትነት ስሜት ተላብሰው በመስራት 'አይችሉም' የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ስብሮ መውጣት ነው'' ብለዋል። በተጨማሪም ከአድሎና ከሙስና በፀዳ መንገድ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን በተግባር ሰርተው ያሳያሉ የሚል ዕምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል። ሌሎች ሴቶችም መማር ከቻሉና አቅማቸውን ካሳደጉ የአሁኖቹ ሴቶች የደረሱበት ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ እምነታቸው እንደሆነም አስረድተዋል። ሴቶች ከወንዶች እኩል 50 በመቶ ስልጣን መጋራታቸው እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል የስነጽሑፍ መምህር ወይዘሮ ሂሩት አድማሱ ናቸው። ሴቶች ወደስልጣን መምጣታቸው በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ተሳታፊ በመሆን የድርሻቸውንና ያላቸውን አቅምና ዕውቀት ተጠቅመው እንዲያገለግሉ ያስችላቸዋል። ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ፣ ለሰላም መረጋገጥና ፖለቲካዊ መረጋጋት የድርሻቸውን በማበርከት አቅማቸውን እንዲያሳዩ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል። ሴቶች 50 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ከፍተኛ የስልጣን እርከን መያዛቸው ከሙስናና አድሉአዊ የፀዳ አሰራር በመዘርጋት ሀገራዊ ግንባታ ወደተሻለ ዕድገት ሊያሸጋግሩ ይችላሉ። የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ስልታዊ በሆነ መልኩ መፍትሄ ለመስጠትና ለሀገራቸው ዕድገትም የድርሻቸውን ለመወጣት ሹመቱ በጎ ተፅዕኖ እንዳለውም አስረድተዋል። የሴቶች ወደከፍተኛው ስልጣን መምጣት ተከታይ ሴቶች ጊዜያዊ ችግሮችን ተቋቁመው ትልቅ ቦታ እንደርሳለን ብለው እንዲያስቡ ትልቅ ምሳሌ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡም ምሁራኑ አስረድተዋል።