በጋሞ ጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች በነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

81
አርባ ምንጭ ጥቅምት 8/2011 በጋሞ ጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች በነዋሪዎች መካከል ትላንት በተፈጠረ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያይቆብ አባይነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተፈጠረው ግጭት በስለት የተወጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ከሁለቱም ቀበሌዎች ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በግጭቱ ምክንያት ከ41 በላይ ቤቶች በቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የግጭቱ መንስኤ በሁለቱ ቀበሌዎች አዋሳኝ በሚገኝ ትምህርት ቤት የይገባኛል ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል። ግጭቱን ለማስቆም፣ ህብረተሰቡን ለማረጋጋትና የግጭቱን አነሳሾች ለመያዝ የአከባቢው ጸጥታ ኃይሎች ከክልልና ፌዴራል ፖሊሶች ጋር በመሆን እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸ ነዋሪዎች በሳውላ አጠቃላይና ወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም