መንግስት ግጭትን አስቀድሞ ለማምከንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ግጭትን አስቀድሞ ለማምከንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 መንግስት የግጭት አቅሞችን አስቀድሞ ለማምከንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በመገኝት የመንግስታቸውን አቋም ለምክር ቤቱ ያሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከሰቱ የማጎሳቆል፣ የግድያና የማፈናቀል ችግሮች አስነዋሪና ጭካኔ የታየበት እንደነበር አስታውሰዋል። ችግሮቹ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ወገን በወገኑ ላይ ጭካኔ ያሳየበትና ኢትዮጵያም እንደ አገር የተፈተነችበት መሆኑንም ተናግረዋል። ''ችግሩቹ የፖለቲካ ዓላማ ያለውና የመንግስትን አቅጣጫ ለማስቀየር ታቅደውና ጠተንተው ሲሰሩ ነበር'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈፀም የተፈፀሙ ችግሮችን እንደ ዘር ማጥፋት አድርገን መቁጠር እንደማይገባ አስገንዝበዋል። በየቦታው በተፈፀሙ አሰቃቂና አስነዋሪ ወንጀሎች ተጎጂ ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ ችግሩን የዘር ጥቃት አድርጎ መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል። እየተስተዋለ ያለው የስርዓት አልበኝነትና የህግ የበላይነት የማስከበር ፈተና እንደ አገር ህዝብና መንግስት ተጋግዞ መሻገር ካልተቻለ የአገር ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ጠቁመዋል። በመሆኑም ህዝቡና መንግስት ተባብረው ፈተናውን ለመሻገር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። "ኃይል የመጠቀም ስልጣን የመንግስት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንጋ ፍትህ መስጠት የአገሪቱን የፍትህ ስርዓት አደጋ የሚጥል መሆኑ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የሚፈፀሙ ግጭቶች ማስቆም፣ ግጭት የመፍጠር አቅም ያለባቸው አካባቢዎች በመለየት ማምከን እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚሉ ዘርፎች ከፍሎ መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር በጥናት የተደገፈ ስራ እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ህዝብም የሰላም ባለቤትና ዘብ መሆኑን አውቆ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ኃላፊነት ወስዶ እንዲሰራ አሳስበዋል። "በጉልበት ህግ ማስከበር ቢቻል ኖሮ ደርግ አይወድቅም ነበር" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ከማስተማር ጨምሮ ችግሮችን ህዝብ ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት እየሰራ ነው'' ብለዋል። ከደረቅ ወንጀሎች ውጪ ባለፉት ወራት በተፈፀሙ ወንጀሎች ከ1ሺህ700 በላይ ሰዎች ለህግ መቅረባቸውን ገልፀው መንግስት ወንጀለኞች ወደ ህግ ማቅረቡን በጥናት እየተመሰረተ የሚቀጥልበት ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። "አዲስ አበባን ማዕከል አድርጎ በማመፅ መንግስት ለመቀየር ተቃዶ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሷል" ብለዋል። ይሄም ያለው አሰራር ደካማ በመሆኑ የሚፈጠር ስለሆነ ወጣቶቹ ለለውጡ መስዋእት እንደከፈሉ አድርገው እንዲቆጥሩት አሳስበዋል። መንግስት በአገሪቱ በሚፈፀሙ ወንጀሎች እጃቸው ያለበትን ሰዎች በተመለከተ ከሳምንት በኋላ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።