ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 107 ሚሊዮን በላይ ደርሷል

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ107 ሚሊዮን በላይ ደርሷል ተባለ። የህዝብ ቁጥር እድገትን ተከትሎ የሚገጥመውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የቤተሰብ ምጣኔን ማስፋፋት እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ስነ-ህዝብ ፈንድ አሳስቧል። የመንግስታቱ ድርጅት የስነ-ህዝብ ፈንድ የዘንደሮውን የዓለም ህዝብ ቁጥር እድገት የተመለከተ ሪፖርቱን ትናንት በአዲስ አበባ ይፋ አደርጓል። በአለም አቀፍ ደረጃ የሰዎች ውልደት መጠን እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም የህዝብ ቁጥር ብዛት ግን ማሻቀቡን ቀጥሏል ሲል ነው ሪፖርቱ ያመለከተው። በሪፖርቱ መሰረት በአሁኑ ወቅት የዓለም ህዝብ ብዛት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ ከአንደ ቢሊዮን በላይ ነው። ሪፖርቱን ያቀረቡት የስነ-ህዝብ ፕሮግራሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሆርዶፋ እንዳሉት ዛሬ ባላደጉት የአለም አገራት ከ214 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሴቶች ላልተፈለገ እርግዝና ይዳረጋሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም በማህበረሰቡ ዘንድ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት የማግኘትና በአግባቡ የመጠቀም እድሉም ሆነ ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት በ155 አገራት ውስጥ ባካሄደው ጥናት መሰረት የውልደት መጠን በአማካይ አንድና ከዚያ በታች እየቀነሰ የመጣባቸው አገራት ግማሽ ያህሎቹ ብቻ መሆናቸውንም አስረድተዋል። የውልደት መጠን በአማካይ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 9  የተመዘገበባቸው አገራት ደግሞ 30 አገራት መሆናቸውም ተመልክቷል። ቀሪዎቹ 43 አገራት በአማካይ አራትና ከዚያ በላይ ልጆች የሚወለድባቸው አገራት ሲሆኑ ከነዚህም መካከል 38ቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው። "ቤተሰብ ሊኖረው የሚገባውን የልጅ ቁጥር የመወሰን መብት አለው፤  ሴቶች ደግሞ እርግዝናን የመከላከልና የማዘግየት ሙሉ መብት አላቸው" ያሉት አቶ ደረጀ የዚህ ዓይነቱን መብት ጥቅም ላይ መዋል ያለበት ግን በእውቀትና በእቅድ ላይ በመመስረት መሆን አለበት ብለዋል። ቤተሰብ በፍላጎቱና በአቅሙ ልክ ቤተሰብ ካልመሰረተ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሆነውን የወጣቶች ስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት መፍታት ከባድ ያደርገዋል ይላሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛትም በዓመታዊ የእድገት ምጣኔ መሰረት በተካሄደ ስሌት በዚህ ዓመት ከ107 ሚሊዮን ልቋል። በኢትዮጵያ ያለው የወሊድ ምጣኔ በከተማ 2 ነጥብ 3፣ በገጠር ደግሞ 5 ነጥብ 2 መሆኑን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው። መንግስት በአሁኑ ወቅት ለስነ ህዝብ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የብሄራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሺነር አቶ ጌታቸው አደም ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት መንግስት በወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች የዛሬ 18 ዓመት ገደማ 4 በመቶ ብቻ የነበረው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ በአሁኑ ወቅት ወደ 36 በመቶ ደርሷል። የወሊድ ምጣኔውም ከ6 ነጥብ 4 ወደ 4 ነጥብ 6 ዝቅ ብሏል። የተገኙት ስኬቶች እንደተጠበቀ ሆኖ  ብዙ ሌሎች የሚቀሩ ተግባራት መኖራቸውንም ምክትል ኮሚሽነሩ ይናገራሉ። እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ሁሉም ሰው ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን በመጠቀም በሚፈልገበት ወቅት ብቻ እንዲወልድ የሚል እቅድ በዘላቂ ልማት ግቦች ተቀምጠዋል። በፆታዊ ጥቃት፣ በአስግድዶ መድፈርና ያለ እድሜ ጋብቻ ላይም ጠንከር ያሉ ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም