ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

ሶዶ ጥቅምት 8/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የትምህርት ዘመን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል መዘጋጀቱን የሶዶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡ ከነዋሪዎቹ የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ፎረም አስተባባሪ አቶ ሚልኪያስ ኦሎሎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአገር ግንባታ ሚና እንዳላቸው አመልክተው፣ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ ዕድገት ያለ ትምህርት ለዉጥ ያለ ሰላም ስለማይታሰብ በአካባቢዉ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት በዚሁ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት በተለየ መልኩ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹን ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት አገራዊ አንድነትን በሚያጠናከር መልኩ  ለመቀበል ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲዉ የአምስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪና የሰላም ፎረም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንት ተማሪ በረከት አፈወርቅ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታን ለማረጋገጥ ዝግጅት መደረጉን ተናግሯል፡፡ የተማሪዎቹን ቅበላ አቀባበሉን ለማሳካት ከከተማው ወጣቶችና ከተማሪዎች ኅብረት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን  አስታውቋል፡፡ የወላይታ በጎ ፈቃደኞች ማህበር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መምህር ተከተል ላበና በበኩሉ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ የሚገቡ ተማሪዎች የእንግድነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም 200 የሚሆኑ የማህበሩ አባላት በሁሉም የከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታውቋል። በዩኒቨርሲቱ የተማሪዎች ጉዳይ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ጉልፎ ዩኒቨርሲቲው የዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ  በሚያስቀጥል መልኩ አከናውኗል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ኅብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር፣በመከባበርና በመቻቻል መንፈስ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ክበባት ተግባቦትንና አገራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እንደሚደራጁም ተናግረዋል፡፡ ከንግዱ ማህበረሰብና ከከተማው አስተዳደር በመመካከር ለሱሶች አጋላጭ የሆኑ የንግድ ተቋማትን ከዩኒቨርሲቲው አካባቢ እንዲሰኑ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ከተማዋ አቅጣጫ የሚያሳዩ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በማደራጀትና ተሽከርካሪዎች ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን  ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲዉ ሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሳሚኤል ሳርካ ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሺህ 500 መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎች ለመቀበል የአቀባበል ኮሚቴ መቋቋሙን  ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲውን  መማር ማስተማሩን ሂደት የተሳለጠና ውጤታማ ለማድረግ የሰው ኃይል አደረጃጀትና የመምህራን ቅጥር መካሄዱን ገልጸዋል። የተማሪዎች ምዝገባ በኮሌጆች ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁንም አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪና የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ከጥቅምት 10 -12/2011 ነባር ተማሪዎችን፣ ከጥቅምት 13-14/ 2011 የአዲስ ተማሪዎች ምዝገባ  እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በማታና በክረምት የትምህርት መርሃ ግብር ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ነው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም