ቀጥታ፡

አዲሱ የሚኒስትሮች ሹመት ለሴቶች የተሰጠው አገርን የመምራት ኃላፊነት ማሳያ ነው - የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት

መቀሌ ጥቅምት 7/2011 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በጸደቀው 20 የሚኒስትሮች ሹመት ግማሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ለሴቶች የተሰጠውን አገርን የመምራት ኃላፊነት ማሳያ  መሆኑን የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ አዲስ የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙም በኢትዮጰያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ችግር ወደ ቀድሞው ቦታ እንዲመለስ ከማድረግ አንጻር  አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን ያላቸውን እምንነት ገልጸዋል፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት እንደገለጹት ሴት አመራሮች ባሳዩት የስራ ብቃት፣ የትምህርት ዝግጁነትና ታታሪነት ለዚህ ዓይነቱ ከፍተኛ አገርን የመምራት ኃላፊነት  በመብቃታቸው እጅጉን መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ፋጢማ ሂቡ እንደተናገሩት "ቀደም ሲል በቃል ሲነገር የነበረው የሴቶችን የስልጣን ተሳትፎ 50 በመቶ እናደርሳለን ተስፋ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት እውን ሆኗል" ብለዋል፡፡ ''ሴት ሚኒስትሮች የተሰጣቸውን ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ እምነት አለኝ'' ያሉት ወይዘሮ ፋጢማ ቀደም ሲል ለከፍተኛ የስልጣን ቦታ የሚታጩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ  እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ''ሴቶችን ወደ ከፍተኛ አመራር የማምጣት ሂደት በየክልሎችም በቀጣይ ለሚካሄዱ ሹመቶች በተሞክሮነት እንደሚወሰድ ተስፋ አለኝ'' ብለዋል፡፡ አዲሱ የሴት ሚኒስትሮች ሹመት ‘‘ሴቶች መምራት አይችሉም‘‘  የሚለውን ኋላቀር አባባል የሚቀይር እንደሆነ ወይዘሮ ፋጢማ ተናግረዋል፡፡ ''የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ አሁን ካለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ አስፈላጊ ነው'' ያሉት ወይዘሮ ፋጢማ "በአገራችን አስተማመኝ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ ባለፈ ለአከባቢው ቀጠና ሰላም መረጋገጥ እጅግ ጠቃሚ ነው" ብለዋል። የክልሉ ምክር ቤት አባልና የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል መምህርት እቴነሽ ገብረኪዳን በበኩላቸው 50 በመቶ ያህል ሴቶች ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሴቶችን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ነው። በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው ሴቶችን በብዛት ወደ አመራር የማምጣቱ አሰራር ወደ ክልሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ መውረድ እንደሚገባ አሳስበዋል። ‘‘ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ‘‘ ያሉት የክልሉ ምክር ቤት አባል የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ አገራችን እየገጠማት ያለውን የሰላም መደፍረስ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ የህግ ልዕልና ጥሰትና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ግጭትና ሁከት ለመፍታት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ በትግራይ ክልል የአሕፈሮም ወረዳ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ዛፉ ጣሰው በበኩላቸው አዲሱ የሚኒስትሮች ሹመት የሴቶችን የዓመታት የመብት ጥያቄ እውን ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰላምን ማረጋገጥ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው ለሴቶች ነው ያሉት ወይዘሮ ዛፉ፣አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም