ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች "ሜድ ኢን ኢትዮጵያ" በተሰኘ መለያ አገራቸውን ለማስተዋወቅ ተስፋ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች "ሜድ ኢን ኢትዮጵያ" በተሰኘ መለያ አገራቸውን ለማስተዋወቅ ተስፋ አድርገዋል
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች በኢትዮጵያ የተመረተ "ሜድ ኢን ኢትዮጵያ" በተሰኘው መለያ አገራቸውን ለማስተዋወቅ ተስፋ ሰንቀዋል። ዲዛይነር ሳምራዊት መርሲኤሓዘን ኢትዮጵያ ውሰጥ የተሰራ "ሜድ ኢን ኢትዮጵያ" የተሰኘ መለያን የያዙ ቦርሳዎችና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን በማምረት አገሯን የማስተዋወቅ ራዕይ ይዛ እየሰራች ትገኛለች። በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ እየተባለች ለዘመናት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከቆዳ ውጤቶች እምብዛም አለመጠቀሟ ያስቆጫታል። እንደ ዲዛይነሯ አገላለጽ አሁንም ቢሆን በቁጭት ከተሰራ በእንስሳት ሃብት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ በተመረቱ የቆዳ ውጤቶች አገርን ለማስጠራት ጊዜው አልረፈደም። ለዚህ የእሷ የቆዳ ቦርሳ፣ ምንጣፍና ሌሎች ምርቶች ተደራሽ በሆኑባቸው አገራት ያለውን ተቀባይነት በማንሳት ታብራራለች። ለዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ምርት ይዛ ስትወጣ ምርቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትንም እየሸጠች መሆኑን እንደሚሰማት ነው የተናገረችው። ስራዋን ከጀመረች ስድስት አመታትን ያስቆጠረችው ዲዛይነሯ፤ ጀርመን፣ ጃፓንና ሆላንድ ምርቷን ከምታቀርብባቸው አገሮች መካከል ሲሆኑ በቀጣይም የዱባይና እንግሊዝ ገበያን ለመድረስ እቅድ አላት። የውጭ ገበያን ሰብሮ ለመግባት መጀመሪያ የራሳችንን መቀበልና የራሳችንን ማድነቅ መጀመር አለብን የሚል ሃሳብም አንስታለች። በቆዳ ምርቶች ያደጉ አገሮች ለዲዛይን፣ ለአሰራርና አጨራረስ የሚጠቀሙበትን ዘዴ ልምድ በመውሰድ መወዳደር አለብን የሚል እሳቤም አላት ዲዛይነሯ። "በውጭ ባህል ጥገኛ ከመሆን የብሔር ብሔረሰቦችን የአለባበስ ስርዓት ከዓለም አቀፍ ፍላጎት ጋር በማመጣጠን መለያ በማድረግ ልንታወቅበት የምንችል የገበያ ዘርፍ ነውም" ስትል ትገልጻለች። የቀደምት ኢትዮጵያውያን እናቶች መገለጫ ከሆነው "ፈትል" በተሰሩ የአገር ባህል ልብሶችም ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ ተስፋ ማድረጋቸውን "የፈትል ዲዛይነር" ሽያጭ ሰራተኛ ወጣት ፌቨን ተስፋዬ ትናገራለች። የኢትዮጵያ ፈትል በማንኛውም ሰዓት ሊለበስ በሚችል መልኩ በማምረት አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ምርቱን ካገኙ በጉጉት እንደሚወስዱ ታዝባለች። ልብሱ የተሰራበት ጥሬ እቃ ከፈትል መሆኑ በተለያዩ አገራት አድናቆትን እያገኘና ባህልን እያስተዋወቀ መሆኑንም ትናገራለች። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ዲዛይነር ቁንጅና ተስፋዬ ዘወትር የሚለበሱ የኢትዮጵያን ባህል የሚገልጹ ልብሶችን በመስራት ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች። የምትሰራቸው አልባሳት የኢትዮጵያን አንዱን ብሔረሰብ አለባበስ በሚገልጽ መልኩ በመሆናቸውም በእያንዳንዱ ልብስ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ባህል እያስተዋወቀች መሆኗን ተናግራለች። ከዚህ በፊት በዓለም ላይ የተሰሩት የአለባበስ ዲዛይኖች እየተደጋገሙ በመሆናቸውና አሁን አሁን እነሱ በሰሩት ዲዛይን መሰረት ዓለም ወደ አፍሪካ ፊቱን እያዞረ መሆኑን በመግለጽ ይህን እድል አገራችንን ለማስተዋወቅ መጠቀም አለብን የሚል አስተያየትም ሰጥታለች።