በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ የሙያ ስልጠና መርሃ ግብር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ የሙያ ስልጠና መርሃ ግብር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የሙያ ስልጠና መርሃ ግብር ይፋ ሆነ። በጀርመን ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ድጋፍ የሚከወነው ፕሮግራሙ ከተለያዩ አገራት ተፈናቅለው በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችና ስደተኛ ተቀባይ አካባቢ ማህበረሰብ ክፍሎችን የሙያ ክህሎት ስልጠናዎች ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። 'ጥራት ያለው የሙያ ስልጠናና የስራ እድል በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችና ተቀባይ ማህበረሰቦች' የተሰኘውን መርሃ ግብር በሙከራ ደረጃ ለመጀመር አዲስ አበባ በሚገኘው የንፋስ ስልክ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዛሬ ይፋ ሁኗል። ለመነሻ በሶማሌና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በንፋስ ስልክ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችና ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በእንጨት ስራ፣ በብየዳና በግብርና መስኮች የክህሎት ስልጠና ይሰጣቸዋል። በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር 2022 የሚጠናቀቀው መረሃ ግብሩ የ6 ሚሊዮን 500 ሺህ ዩሮ በጀት የተመደበለት ሲሆን ከ1 ሺህ 500 በላይ ስደተኞችና ኢትዮጵያዊያንን የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል። በትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳህለስላሴ ተክሌ እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞች በቴክኒክና ሙያ ስልጠናና የስራ እድል የሚያገኙበትን እድል መፍጠር የረጅም ጊዜ እቅዱ መሆኑን አንስተዋል። ይሁንና በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ብዛትና ስፋት ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት አቅም ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስኬታማዋ ጀርመን ፕሮግራሙን በመጀመሯ አድንቀዋል። የመርሃ ግብሩ ስራ አስኪያጅ ኒኮላስ ደሜን ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሁለተኛነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በመቀበል የምታከናውነውን ተግባር አድንቀዋል። በተለይም ወጣት ስደተኞች ቀጣይ ህይወታቸውን ለመምራት የሚችሉበት ሙያ እንዲኖራቸው ደግሞ ጀርመን የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል። መርሃ ግብሩ ሶስት አንኳር ተግባራት እንዳሉት ጠቅሰው ስደተኞች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የስልጠና ተቋማትን ማጠናከር፣ የስራ እድል የሚፈጥሩ ጥራት ያላቸው ስልጠናዎችን መስጠትና የማሰልጠኛ መሳሪዎችን ማሟላት ቀዳሚ ተግባራት እንደሆኑ ተናግረዋል። በስደተኞች መጠለያ አካባቢዎች የክህሎት ስልጠና አሰልጣኞችን ቁጥርና የስልጠናውን ተደራሽነት ማስፋት ሌላው ተግባር መሆኑን እንዲሁም ስደተኞችና ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በጋራ የሚሰሩባቸው የስራ እድሎችን ማመቻቸት፣ ልምድና ተሞክሮ ማስፋትንም ጠቅሰዋል። ፕሮግራሙ ውጤታማ እንዲሆን ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከፌዴራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቃልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ቀጥሎ ስደተኞችን በመቀበል ከአፍሪካ ሁለተኛ ስትሆን አሁን ላይ ከ900 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎችን አስጠልላለች።